



























የደቡብምዕራብኢትዮጵያህዝቦችክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዚህ አምድ አጠቃላይ የክልላችንን ገጽታ የሚያሳይ ፅሁፍ እንዲሁም ከክልላችን ዞኖች አንዱየ ሆነውን የምዕራብ ኦሞዞንን ቃኝተን ለውድ አንባቢዎቻችን አድርሰናል፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ከክልላችን ዞኖች አንዱ የሆነውን የካፋ ዞንን እንቃኛለን፡፡መልካምንባብ!
የካፋ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልለዊ መንግስት ከሚገኙ ስድስቱ ዞኖች አንዱ ሲሆን በ12 ወረዳዎችና በ5 ከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ ዞን ነዉ። ከጠቃላይ በዞኑ ስር የሚገኙ የቀበሌዎች ብዛት 350 ሲሆን ከነዚህም 52 የከተማ ቀበሌዎች እና 298 የገጠር ቀበሌዎች በዞኑ ይገኛሉ። ዞኑ በሰሜንና በሰሜን ምስራቅ ኦሮሚያ ክልል ፣በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ቤንች ሸኮ ዞን ፣በሰሜን ምዕራብ ሸካ ዞን ፣ እና በምስራቅ ኮንታ ዞን ያዋስነዋል ። የካፋ ዞን መዲናና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአሰተዳደርና የፖለቲካ መቀመጫ የሆነች ቦንጋ ከተማ ከመዲናችን አዲስ አበባ በ449 ኪ/ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች ።
የዞኑ ጠቅላላ የቆዳ ስፋት 10,602.7 ስ.ኪ.ሜትር ሲሆን ከፍታዉ ከባህር ወለል በላይ 501 ሜትር ደቡባዊ ዴቻ ጮጫ ዝቅተኛ አከባቢ ጀምሮ እስከ ምስራቃዊ ጠሎ ውስጥ 3348 ሜትር ሾትራ ተራራ ላይ ነዉ። የዞኑ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡን ስንመለከተ ከምድር ወገብ በላይ 6’24 እስከ 8’13 ሰሜን ላትቲዩድ እና ከግሪንዊች ሜሪዲያን 35’48 እስከ 36’78 ምስራቅ ሎንግቲዩድ ድረስ ይዘረጋል ።
በዞኑ የሚለማ መሬት በሄ/ር 545 ሺ 732.73 ሄ/ር፣ የማይለማ መሬት 11 ሺ6.92 ሄ/ር፣ በደን የተሸፈነ መሬት 382 ሺ 943.47 ሄ/ር፤በሌሎች የተያዘ መሬት 44ሺ 534.73 ሄ/ር፣ በዉሃ የተሸፈነ 17 ሺ 494.98፣ ወደፊት ሊለማና ሊታረስ የሚችል መሬት 45ሺ 309.78 ሄ/ር ነዉ፡፡ የዞኑን የዝናብ መጠን በተመለተ ዓመቱን በሙሉ ዝናብ የሚዘንብበትና ዝናብ የማያጥረዉ ዞን ከመሆኑ ጋር ተያይዞየግብርና ምርትና ምርማነት እንዲሁም በእርባታ ሥራዎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚታወቅ አካባቢ ነዉ፡፡
ከዞኑ ከጠቃላይ ቆዳ ስፋት 8 ሺህ ደጋ ፣70 ሺህ ወይና ጀጋ እና 22 ሺህ ቆላ የአየር ፀባይ አለዉ ። ቆላ ከ500 እስከ 1300 ሜትር ከፍታ ላይ ሲሆን ወይና ደጋ 1300 እስከ 2200 ሜትር ከፍታ እንደዚሁም ደጋ ከ2200 እስከ 3000 ሜትር ከፍታ አለዉ ። ከላይ ከተዘረዘረዉ የቆዳ ሽፋን ከ760 ሄ/ር በላይ የሚሸፍነዉ የባዮስፌር ጥብቅ ደን ቦታ በሰኔ 2010 እኤአ በዩኔስኮ በአለም የብዝሃ ህይወት ጥብቅ ቦታ ሆኖ ተመዝግበዋል።
የ1999 ዓ.ም የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤትን መሠረት በማድረግ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ባደረገው ትንቢያ በ2016 የበጀት ዓመት የዞኑ ህዝብ ብዛት 1,444,996 (713,441 ወንድ እና 731,554 ሴት) እንደሆነ ይገመታል፡፡
በካፋ ዞን ዉስጥ ሶስት ነባር ብሔረሰቦች ያሉ ሲሆን እነሱም ካፈቾ፣ናይ እና ፃራ ብሔረሰቦች ናየዉ ።ከነዚህ ነባር ብሔረሰቦች በተጨማሪ በዞኑ ሌሎች የኢትዮጵያ በሔር ብሔረሰቦች ከዞኑ ነባር ብሔረሰቦች ጋር ተጋብተዉ ተዋህደዉና ተጋምደዉ በመከባበርና በመተሳሰብ አብሮ ይኖራሉ።
የካፈቾ ብሔር የናይ እና ጻራ ብሔረሰቦች ተቻችሎ፣ተከባብሮ፣ተጠያይቆና ተደጋግፎ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠሩና የተጋመደ ማንነት ያላቸውናቸው።እነዚህ ብሔረሰቦች ከታላለቆች የወረሱት የለቅሶ፤የሰርግ፣ የአመጋገብ፣ የአለባበስ የጭፈራና ሌሎች የየራሳቸው ባህል አሏቸው። የየራሳቸው ባህል ቢኖራቸውም አንዱ የሌላውን ባህል በማክበርና በመተሳሰብ አንዱ የአንዱን ያደምቃል፤አንድነታቸውን የሚገልጹበት ልዩ ምልክት አላቸው።
የፃራ ብሔረሰብ በካፋ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ሶስት ነባር ብሔር/ ብሕረሰቦች ውስጥ አንዱ ሲሆን የሚገኘዉም በካፋ ዞን ጎባ ወረዳ ነዉ፡፡ የፃራ ብሔረሰብ መተዳደሪያቸዉ በእርባታ ፣።ቡና ፣።ቅመማቅመም ፣ ጤፍና ስራስሮችን በማምረት ነዉ ።
የፃራ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ማህበራዊና ጂ ኦ ፖለቲካዊ አደረጃጀት ያለዉ ነበር፡፡ጥንት ብሔረሰቡ የሚተዳደረዉ በራሱ ንጉሥ ሆኖ በጊዜ ሂደትም ተጠርነቱ ለካፋዉ ንጉስ ተጠሪ ለሆነው ጎባራሻ እንደነበር የታርክ ፀሀፊዎች ይገለጻል፡፡ የፃራ ብሔረሰብ ቋንቋ ፃርኛ (ጻራሴ ኖና) ይባላል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ኢትዮኦማዊ ቋንቋዎች አንዱ ነው ፡፡
ሌላው በካፋ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ሶስት ነባር ብሔር/ ብሔረሰቦች አንዱ የናይ ብሔረሰብ ነዉ ። ብሔረሰቡ በካፋ ዞን ጎባ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ቋንቋቸዉ ከኦሞቲክ የቋንቋ ግንድ የተገኘ ነዉ፡፡ ብሔረሰቡ ዋና መተዳደሪያው ግብርና ሲሆን ጥንታዊ የተደራጀ የፖለቲካና አስተዳደር ስርዓት የነበራቸውና የዳበረ ባህል ያላቸው ናቸው፡፡
የካፈቾ ባህላዊ የንግስና ስርዓትን በተመለከተ ሶስት ስርወ መንግስታት ስርዓትን ያለፈ ሲሆን እነሱም ሚንጆ ፣።ማቶና ማንጆ ስርወ መንግስት ናቸዉ ።ካፈቾ የራሱ የሆነ የንግስናና የምክረቾ ስርዓት ያለዉ ሲሆን ስርዓቱ ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ የንግስና ስርዓት መሆኑን ጥናቶች ያስረዳሉ ።የካፋ ምክረቾ አባላት ወደ አስር የሚሆኑ የተለያየ የስልጣን ደረጃ ያላቸዉ የአሁኑን ዘመናዊ የአስተዳደር ስርዓት የተከተለ ከንጉሱ ጀምሮ ጉጀራሾ ፣ ካተመራሾ ፣ ወፈራሾ ፣ አርችየራሾ ፣ ወዘተ እያለ ወደታች በተዋረድ የሚሰየም የምክረቾ አባላትን ይዞ የተዋቀረ ነዉ ።
በካፈቾ ብሔር ዘንድ የደስታ ጭፈራ ስርዓት በደቦ፣ በሰርግ ፣በምላሽ ፣ በቤት ምረቃ ፣ ወዘተ የደስታ ጭፈራዎችን እየጨፈሩ ደስታቸዉን ይገልፃሉ ።በለቅሶና በሀዘን ጊዜም የአኸባቢ ማህበረሰብ ተሰብስቦ ህቾና ጎሞ የሚባሉ የሀዘን መግለጫ ትርዕቶችን በማሳየት ለሟች ማዘናቸዉንና ለቀስተኞች እንዲፅናኑ ያደርጋሉ ።
በካፋ እንሰት ትልቅ ቦታ የሚሰጠዉ ተክል ሲሆን የአመጋገብ ስርዓት በዋናነት ቆጮ ለምግብነት የሚዉል ሲሆን ለመባያነት አይብ፣ቅቤ፣ስጋና ወተት ወዘተ ምግቦችን አዘወትሮ የሚጠቀሙ ሲሆን የአመጋገብ ስርዓቱ የታላላቆችን ምርቃት በማስቀደም በህብረት ይመገባሉ። እንሰት የካፈቾ ትልቁ ባህላዊ ምግብ ሲሆን ከእንሰት በርከት ያለ የምግብ አይነት ተዘጋጅቶ ለምግብነት ይቀርባል፡፡ እንሰት ተፍቆ ቆጮ ፣ኤትኖ ፣ ዱፖ ፣ ወዘተ ሲወጣ ቂጡ ተቀቅሎ አምቾ ተብሎ ለምግብነት ይቀርባል ፡፡
ቡናና ካፋ የማይነጣጠሉ ታሪካዊ ቁርኝት ያላቸዉ ናቸዉ፡፡ ስለሆነም ቡና የተገአዉ በካፋ ዞን ማኪራ በሚባል አከባቢ ነዉ። ካፋ የቡና መገኛ ምድር እንደመሆኗ የእንግሊዝኛዉ ስም ኮፊ ተብሎ የተሰየመዉ ካፋ ከሚለዉ ስም ተወስደዉ ነዉ ። ቡናን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘዉ ካል አዲ የተባለ ፍየል ጠባቂ እንደሆነ ከታሪክ መፅሐፍት የተገኙ መረጃዎች ያስረዳሉ ። ቡና ከመጠጫነት ባለፈ ለካፋ ማህበረሰብ ዋንኛዉ የኢኮኖሚ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ። ይህንን ታሪካዊ የካፈቾና የቡና ቁርጭትን በተግባር ለማሳየት ሲባል ብሔራዊ የቡና ሙዚዬም በቦንጋ ከተማ ተገንብቶ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እንዲያስተዳድር ተደርጎ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
ባህላዊ የደንና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ በሚለከት ካፋ ከደን ወይም ከእፅዋት ጋር አብሮ ተላምዶና ተስማምቶ የሚኖር ማህበረሰብ ነዉ፡፡በካፈቾዎች ዘንድ ደን ከጥንት ጀምሮ እንደአይን ብሌኑ ተጠብቆና እንክብካቤ ተደርጎ የቆየ ትልቁ ገፀ በረከት ነዉ፡፡ ደን በካፋ ማህበረሰብ በባህላዊ መንገድ በልዩ ትኩረት ተጠብቆ ከልጅ ወደ ልጅ ሲተላለፍ የመጣ ሀብት ነዉ፡፡ይህንንም በዘመናዊ መንገድ አስጠብቆና ተንከባክቦ ለማስቀጠል በዩኔስኮ በጥብቅ ደንነት ተመዝግቦ ተጠብቆና እንክብካቤ ተደርጎለት የሚገኝ ታላቅ ሀብት ነዉ፡፡ ከደኑም በርካታ ጥቅማጥቅሞችን ማለትም መድሃኒት፣ ምግብ፣ የተስተካከለ አየርና ዝናብ ወዘተ እያገኘ ደንን ከእለት ተዕለት ህይወቱ ጋር አቆራኝቶ የሚኖር ማህበረሰብ ነዉ
የእርባታ ስራ በካፋ ህዝብ የሚዘወተር ተግባር ነዉ ።በመሆኑም የጋማ ከብት ፣የቀንድ ከብት ፣ ዶሮ ወዘተ ያረባል ። የከብት እርባታ ስራ ለካፋ ማህበረሰብ ባንካቸዉ ነዉ ቢባል ማጋነን አይደለም ።ጥሬ ገንዘብ በእጅ ከሚያስቀምጥ ከብት ገዝቶ ቢያስቀምጥ ይመርጣል። የካፋ ማህበረሰብ የሚያረባዉን ከበት ለተለያዩ ግልጋሎቶች ማለትም ለምግብነት ፣ ለአልባሳት ፣ ለእርሻ እና ለትራንፖርት ወዘተ ይጠቀማል ። የእርባታ ስራ ደጋማና ወይናደጋማ የካፋ አከባቢዎች በስፋት የሚሰራ ሲሆን በቆላማ የዞኑ አከባቢዎችም በጥሩ ሁኔታ የእርባታ ስራ ይሰራል ።
በካፋ የባህላዊ የዳኝነት ስርዓትን በተመለከተ በሰዎች መካከል የተፈጠሩ ከለመግባባቶችና ሌሎች በደሎች በኦቶና በሽምግልና ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶች ችግሮች ተነቅሰዉ ወጥተዉ እልባት ያገኛል ።በባህላዊ ስርዓት ጉዳዩን መርምረዉ ችግሮችን ለይተዉ በዳይንና ተበዳይን ለይቶ መዳኘት የሚችሉ እዉነትና ሀቅ ላይ የተመሠረቱ የሀገር ሽማግሌዎች ይመረጣሉ ። ባህላዊ ዳኞች በተዘጋጀ ትልቅ ዛፍ ጥላ ስር ይቀመጡና በቅድሚያ የተበዳይን በደል በማድመጥ በዳይ ለምን እንደበደለዉ በመመርመር ጥፋተኛን በመለየት ካሳ ወይም ኑሞ የሚባል ወስኖ በማሰጠት እርቅ እንዲወርድ ተደርጎ የማስታረቅ ስራ ይሰራሉ። ሲቃረኑ የነበሩ አካላት እንደታረቁ ወዲያዉ የተዘጋጀዉን ምግብ በልተዉ ቡና ጠጥተዉ እርቀሰላም አዉርደዉ ወደየቀያቸዉ ይመለሳሉ።
ካፋ የራሱ የሆነ የቡና አፈላል ስነ ስርዓት አለዉ፡፡ ቡና በካፋ ማህበረሰብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠዉ ከየትኛዉም ምግብ ቀድሞ የሚጠራዉ ቡና ነዉ ። ማንኛዉን ተወዳጅና ጣፋጭ ምግብ አቅርቦ ለመመገብ በካፋ ባህል ቡና ጠጡ ነዉ የሚባለዉ ። ቡና ለማፍላት መጀመሪያ ጀንፈል ቡና ይቀሸራል፡፡ የተቀሸረዉ ቡና በፈላ ዉሃ በሚገባ ይታጠባል፡፡የታጠበዉ ቡና በሸክላ ምጣድ በጥሩ ሁኔታ በአግባቡ ይቆላል፡፡ የተቆላ ቡና በቡኔ ቦቶ ተወቅጦ የተገኘዉ የቡና ዱቄት በሸክላ ጀበና በፈላ ዉሃ ላይ ተመጥኖ ይጨመርና በሚገባ እንዲፈላ ይደረጋል፡፡ ቡና እየፈላ እያለ የቡና መጠጫ ከቀርከሃ የተዘጋጀ ትንጃኖ የሚባል ንፁህ ተደርጎ ታጥቦ ይደረደራል የፈላ ቡና ቅቤ ካለ ተጨምሮ ከሌለም አለቅቤ በትንጃኖ ተቀድቶ እጣን ጭሶ የተዘጋጀ ቁርስ ቀርቦ ይጠጣል፡፡
የካፋ ዞን በሁሉም አካባቢዎች በርካታ የቱርስት መዳረሻ ስፍራዎች ያሉት ሰፊ ዞን ነዉ፡፡ ከነዚህም መካከል በቦንጋ ዙሪያ የሚገኝ የባርታ ፏፏቴ፣ የቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዚዬምና ቦንጌ ሻምበቶ፤በዴቻ ወረዳ ጉርጉቶ የኢግዚሔር ድልድይ፣ ማኪራ እናት ቡና፣ ዕድሜ ጠገብ አቢያቴ ክርስቲያናትና ገዳማት፤ቶንገላ አብዱ ሰላም መስጂድ፣ በጌሻ ወረዳ የሚገኝ ኤሌሎ ፏፏቴና ዋሻ እንዲሁም ኑቲቅቲና ዳዳቲ ፏፏቴዎች፣በጊምቦ ወረዳ ዳዲበን ፊል ዉሃ፣ በጨታ ወረዳ የሚገኝ ቢላይ ተራራና የብረት ማዕድን፣ በገዋታ ወረዳ የሳጃ ጥብቅ ደን፣ቃላዲ ዋሻና ገኒ ፏፏቴ፣ በጠሎ ወረዳ ሾሻሞጎና ሽናቲ ኢኖ/ጸበል/፣ በአዲዮ ወረዳ አዲዮ ፏፏቴና ጥብቅ የቀርቀሃ ደን፣ በሺሾእንዴ ወረዳ ወሺ ፏፏቴ፣ በሳይሌም ወረዳ ፈጪ ፏፏቴ እንድሁም በሌሎች ወረዳዎች የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በአጠቃላይ በዞኑ ወደ 138 የሚሆኑ ባህላዊ፣ታሪካዊ፣ተፈጥሯዊና ሰዉ ሰራሽ የቱሪስት መስሂቦችና መዳረሻዎች ያሉ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ የለማ 43 ያልለማ 95 ይሆናል፡፡
