



በሸካ ዞን የቴፒ አጠቃላይ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማሻሻል የሁሉም ማህበረሰብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲፈቱም ተጠይቋል።
የቴፒ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ አስታወሰኝ አዴሎ እንደገለፁት ሆስፒታሉ ከአካባቢው ነዋሪዎች ባሻገር ከአጎራባች ክልሎች እና ዞኖች ለሚመጡ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቀን በአማካይ ከ300 እስከ 400 የሰው ኃይል በላይ እንደሚያስተናግድ ጠቅሰው በዚህም የህክምና ግብዓት አጠቃቀም ላይ ጫና እንደፈጠረ ተናግረዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የገለፁት ስራ አስኪያጁ ለዚህም የውስጥ አሰራሩ በቅንጅት በመመራቱና የማህበረሰቡ የጤና ግንዛቤ ያደገ መምጣቱ አመላካች ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በሆስፒታሉ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ግብዓቶች ረዥም ጊዜ ከማገልገላቸው የተነሳ ለብልሽትና ለጉዳት እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልፀው የጥገናና እድሳት ስራዎችን ጨምሮ አዳዲስ ግብዓቶችን የሟሟላት ስራ የመንግስት፣ የማህበረሰቡና የአጋር አካላት ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል።
አቶ አስታወሰኝ አክለውም የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመድሃኒት እጥረት ጥያቄዎችን እየተፈቱ መሆኑን ገልፀው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከወረዳና ከተማ መዋቅሮች የተሰበሰቡ መዋጮዎች በጊዜው ገቢ እንዲደረጉና ለታለመላቸው ዓላማ መዋል እንዳለበት ተናግረዋል።
አጠቃላይ ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ የተጀመረው የግንባታ ሂደት መቆሙ ለአገልግሎት አሰጣጥ ጫናው የጎላ በመሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለችግሩ መፍትሔ በመስጠት ወደ ስራ እንዲገባም መደረግ እንዳለበት አቶ አስታወሰኝ ጠይቀዋል።
በሆስፒታሉ ሲገለገሉ ያገኘናቸው ታካሚዎችና አስታማሚዎች በሰጡት አስተያየት ሆስፒታሉ የማህበረሰቡን ችግር በመፍታትና የብዙ ሰዎችን ህይወት በመታደግ ላይ መሆኑን ተናግረው በስራው ላይ የተሰማሩ አካላት ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
በሆስፒታሉ በየጊዜው የሚከሰተውን የመድኃኒት እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ቅንጅታዊ ስራና መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የሆስፒታሉ የውስጥ አሰራር ፣ የውስጥ የጤና መገልገያን ጨምሮ አጠቃላይ ጽዳት ለተገልጋይ ማህበረሰብ ምቹ እንዲሆን የሁሉም ማህበረሰብ ድጋፍ የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የራሱን አሻራ ማኖር አለበት ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።
የጤና ባለሙያዎች እና አጠቃላይ የአስተዳደር ሠራተኞች ስነ ምግባር እንዲሁም መስተንግዶ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የተናገሩት የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ይህም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ማለታቸዉን የሸካ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።
በነፃነት ኃይሌ
