የሆቴሉ ስራ መጀመር በክልሉ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ያሳልጣል፦ አቶ ማስረሻ በላቸው

Spread the love

ሌዊ ሪዞርት በቦንጋ ከተማ ያስገነባው ዘመናዊ ሆቴልና ሪዞርት የክልሉን የኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚያሳልጥ መሆኑን ነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በምረቃው ስነ-ስርዓት ወቅት የገለጹት።

ክልሉ ለሆቴልና ኢኮ-ቱሪዝም እንቨስትመንት ምቹ አከባቢ መሆኑን የገለጹት አቶ ማስረሻ የክልሉን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ለመጠቀም በአግልግሎት ዘርፍ የአልሚዎች ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በቦንጋ ከተማ ተገንብተው ለአግልግሎት የበቃው ሪዞርት የቦንጋ ከተማን የአግልግሎት ዘርፍ ከማነቃቃት ባሻገር የከተማውን ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ የጠቆሙት አቶ ማስረሻ ሌዊ እንቨስትመንት ከሆቴልና ሪዞርት በተጨማሪ በቡና ልማት ዘርፍ ተሰማርተው እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ በክልሉ መንግሥት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የሪዞርቱ እውን መሆን የለውጡ መንግሥት ለብዝሀ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሴክተር የሰጠው ትኩረት ውጤት መሆኑን ያመለከቱት የካፋ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ እንዳሻው ከበደ ሪዞርቱ ለዞኑ ተጨማሪ ዕድል ይዞ የመጣ ነውም ብለዋል።

ዞኑ ለቱሪዝም መስዕብ የሚሆኑ በርካታ ጥንታዊ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ እምቅ ሀብቶች እንዳሉት ያብራሩት አቶ እንዳሻው የዞኑ መንግሰት በዘርፉ በልማት ለመሰማራት የሚመጡ አልሚዎችን ለመደገፍ ከመቼም ጊዜ በበለጠ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ እንዳሻው አክለው የሪዞርቱ መገንባት ለከተማው የሚሰጠውን የጎላ አስተዋጽኦ በመረዳት ለማስፋፋያ ይዞታቸውን የለቀቁት የልማት ተነሺዎችን በዞኑ መንግሥት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ለሪዞርቱ ማስፋፋያ ግንባታ የከተማው መንግሥት ለ18 የልማት ተነሺዎች ምትክ ቦታ በማዘጋጀትና ከ21.4 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መክፈሉን የገለጹት የቦንጋ ከተማ ካንቲባ አስማማው አደም በቀጣይ የሪዞርቱ ምዕራፍ ግንባታ የከተማው መንግሥት ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ፕሮጀክት እውን እንዲሆን በየደረጃው ድጋፍና አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና ያቀረቡት የሌዊ ኢንቨስትመንት ጉሩፕ ባለቤትና ስራ-አስፈጻሚ አቶ ወንድይፍራው እንዳሻው የግንባታውን ሂዴት በየጊዜው በመከታተል የሚገጥሙ ችግሮችን በማረም የአከባቢው መንግሥት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የአከባቢው ማህበረሰብ የእንግዳ ተቀባይነት፣ እንክብካቤና ያሳዩት ፍቅር ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወንድይፍራው የቀጣይ ምዕራፍ የሆቴሉን ግንባታ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ድርጅቱ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

ሆቴሉ ከሚሰጠው የተሟላ የሆቴልና ሪዞርት አግልግሎት በተጨማሪ ለበርካታ የየአከባቢው ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የጠቆሙት ስራ-አስፈጻሚ በሀገር ደረጃ የቦንጋ ሌዊ ሪዞርት ስምንተኛ መሆኑን አያይዘው ገልጸዋል።

የካፋ ዞን ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች በሆቴሉ ምረቃ የተለያዩ ስጦታዎችን አበርክተዋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓቱ የክልል፣ የካፋ ዞን እና የቦንጋ ከተማ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣የከተማው ነዋሪዎች እንዲሁም የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *