የማህበረሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የተቀናጀ ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ የኮንታ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

Spread the love

የኮንታ ልማት ማህበር በውስጥ አቅም በተሰበሰበ ከ2 መቶ 15 ሚሊየን ብር በላይ የገዟቸው 5 የግንባታ ማሽነሪዎችን እና ኢሞታ አዳሪ ትምህርት ቤት ዛሬ በይፋ አስመርቋል።

በመረሃ ግብሩ ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ እንደገለጹት ልማት ማህበሩ በመንግስት ያልተሸፈኑ የተለያዪ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በመንግስት ያልተሸፈኑ የልማት ክፍተቶችን ለማሟላት ልማት ማህበሩ የተቀናጀ ጥረት እያደረገ ይገኛል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በዞኑ በስፋት የሚስተዋለውን የመንገድ ተደራሽነት ችግሮችን ለመቅረፍ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

አሁን ላይ የተፈጠረው ይሄው ምቹ ሁኔታ የዞኑን መሠረተ ልማት ችግሮች በዘላቂነት ከመቅረፍ ጎን ለጎን ልማት ማህበሩ ተጨማሪ ሀብት እንዲፈጥር ያስችላል ብለዋል አስተዳዳሪው።

ከማሽነሪዎቹ በተጨማሪ ከ 130 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባ የገንጂ ኢሞታ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ተመርቋል።

አሁን ላይ 79 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ የሚገኘው ይሄው ትምህርት ቤት በዞኑ የትምህርት ጥራትን ለማጎልበት አይነተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጿል።

በልማት ሥራዎቹ ምረቃ የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራን ጨምሮ የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የተጋበዙ የአካባቢው ተወላጆች እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *