




የዘመናት ጥያቄያቸው የሆነው የኔትወርክ አገልግሎት ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን የኮንታ ዞን የኮንታ ኮይሻ ወረዳ የኮይሻ ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል።
የወረዳዉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ያነጋገራቸዉ የከተማዋ ነዋሪዎች በአካባቢው በ21ኛው ክፍሌ ዘመን የኔትወርክና መብራት አገልግሎት አለመኖሩ የዘውትር ጥያቄያቸው እንደነበረና በውስጣቸው ቅሬታ ፈጥሮ የቆየ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአካባቢው ኔትወርክ ባለመኖሩ የተለያዩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን የገለፁት የከተማዋ ነዋሪዎች ለአብነት የባንክ አገልግሎትን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም አከባቢው ታላላቅ ፕሮጄክቶች መገኛ ከመሆኑም ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የኔትወርክ እጥረትና መብራት አለመኖር አከባቢው ያለውን እምቅ ሀብት በአግባቡ ተጠቅሞ እንዳይሻገርና እንዳይበለጽግ ትልቅ ማነቆ ሆኖ መቆየቱንም ገልጸዋል።
በመሆኑም የረዥም ጊዜ ጥያቄ ከነበሩ ከመሠረተ ልማት ጥያቄዎች አንዱና ቁልፍ የሆነው የኔትወርክ ችግር መፈታቱ በሁሉም ዘርፍ ብልጽግና ለማረጋገጥ በር ከፋች መሆኑን ተናግረው በዚህም መደሰታቸውን ገልጸዋል
በመጨረሻም የህዝቡ የዘውትር ጥያቄ ለመልማት ያለው ፍላጎት መሆኑን ተገንዝበው ምላሽ በመሰጠቱ የወረዳ አስተዳደርን ጨምሮ የዞንና የክልል መንግስት፣ ባለድርሻ አካላትና ለዚህ ድል የበኩላቸው አስተዋጽኦ ላበረከቱት ሁሉ የላቀ ምስጋናቸውን ማቅረባቸዉን የዘገበዉ የኮንታ ኮይሻ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ነው።
