20ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት አህጉራዊ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

Spread the love

20ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት አህጉራዊ ኮንፍረንስ ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት በአፍሪካ ኅብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ኮንፈሰንሱ “የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ፤ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

ኮንፈሰንሱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ጨምሮ የአለም የቴክኖሎጂ እድገት፣ ሰላምና ጸጥታ፣ የሀገራት የንግድ ፖሊሲዎች እና የአየር ንብረት ለውጥ በሰራተኞች ደህንነት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚኖራቸውን አዎንታዊ እና አሉታዊ ተጽእኖዎች በመፈተሽ የመፍትሄ ሀሳብ ለማፍለቅ እንደሚያስችል ተገልጿል።

በተጨማሪም ኮንፈሰንሱ የልማት ሥራዎች የአካባቢ ጥበቃን፣ የማህበረሰብ ደህንነትን፣ አካታችነትን እና ዘላቂ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደረግ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ የ20ኛው የዓለም ዓቀፍ የሥራ ድርጅት አህጉራዊ ኮንፈረንስ እያስተናገደች ሲሆን፤ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በአካታች እና ዘላቂ ልማት ረገድ እያስመዘገበች ያለችውን ውጤት ተሞክሮ ታካፍላለች ተብሏል።

በዚህ ኮንፈረንስ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ሚኒስትሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የሲቪክ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የአሰሪዎች እና የሰራተኞች ፌደሬሽኖች ተወካዮች እንዲሁም የዘርፉ ምሁራንና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በየሁለት ዓመት የሚካሄደው ይህ አህጉራዊ ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው በ2023 በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው 19ኛው ኮንፈረንስ ወቅት ነበር።

በ1919 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር እንደተመሠረተ የሚነገርለት የአለም የስራ ድርጅት (ILO) ወደ 187 አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን በመላው ዓለም ከ40 በላይ ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዳሉትም መረጃዎች ያመላክታሉ ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *