





የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለዉጥ ቢሮ በክልሉ በተለያዩ የማዕድን ሀብት ያላቸው አካባቢዎች ላይ ህጋዊ ፈቃድ ወስደው ማዕድን ስራ ላይ የተሰማሩ ማህበራትና ድርጅቶች በገቡት ውል መሠረት የአካባቢ ጥበቃና የማህበራዊ ደህንነት ህጎች ተፈጻሚነት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የቢሮ ኃላፊው ዶክተር ኢንጂር አስራት ገ/ማርያም ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑንና በዋናነት የከርሰምድር ሀብት የሆነው የወርቅ እና የድንጋይ ከሰልን ሀብት ወደ ውጤት ከመቀየር አንጻር የነበረው እንቅስቃሴ አናሳ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሁን የለውጡ መንግስት በሰጠው ዕድል በርካታ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ስራዎች በመሰራታቸው በርካታ ባለሀብቶችን በማሰማራት በዘርፉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ የማዕድን ሀብት ህጋዊ ፈቃድ ወስደው ማዕድን ስራ ላይ የተሰማሩ ማህበራትና ድርጅቶች በገቡት ውል መሠረት የአካባቢ ጥበቃና የማህበራዊ ደህንነት ህጎችን ተፈጻሚ የማድረግ ስራ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የተፈጥሮ ሀብቱን ለመጠቀም በአካባቢው ላይ የሚመጡ ጉዳቶችን ለማረምና ለማስተካከል የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል በማዕድን ስራዎች ላይ ለሚሰማሩ አካላት ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግም ዶክተር ኢ/ር አስራት ገ/ማርያም አስረድተዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ የሆኑት አቶ ንጉሴ ወ/ጊዮርጊስ እንዳሉት፣በሀገራችን የነበረው የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን አውስተው ከለውጡ መንግሥት ወዲህ ብዘሀ ኢኮኖሚ ዘርፍ በመከተላችን በአካባቢያችን በተለይ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ተከትሎ የደን ስራችንን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የተፈጥሮ ጸጋውን መጠበቅና መንከባከብ እንዲሁም ህብረተሰቡ ከዘርፉ ጥቅም እንዲያገኝ የማድረግ ተሳትፎውን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
በመድረኩ የአካባቢ ጥበቃና የማህበራዊ ደህንነት ህጎችን ተፈጻሚ ማድረግን ያለመ የመነሻ ጽሁፍ በቢሮዉ ምክተ3ል ኃላፊና የአካባቢ ጥበቃ፣አየር ንብረት ለዉጥ ዘርፍ ኃላፊ በሆኑት አቶ ደምሴ ደንቦ ቀርቦ ዉይይት እኡተደረገበት ይገኛል።
በካሳሁን አሰፋ
