በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በሔናን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዲፓርትመንት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ወደ ስራ ለማስገባት ምክክር ተካሄደ

Spread the love

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቻይና ሄናን ግዛት ጄንጆ ከተማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዲቪዥን ጋር የተፈረሙ ስምምነቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ምክክር ተካሄደ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ከቻይና ሔናን ግዛት ጄንጆ ከተማ ልዑካን ጋር ተወያይተዋል።

ውይይታቸውም በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በሔናን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዲፓርትመንት መካከል ባሳለፍነው ጥቅምት የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ወደ ስራ ማስገባት ላይ ያተኮረ ነው።

ስምምነቱ የምርምር ስራዎችን በጋራ መስራት፣ የአቅም ግንባታ፣ የተመራማሪና ምርምር ውጤቶች ልውውጥ ማድረግ እንዲሁም አውደ ጥናቶችን በጋራ ማካሄድን ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በዚህ ወቅት እንዳሉት የትብብር የምርምር ስራዎቹ በዋናነት በአካል ጉዳተኞች እና በአእምሮ ጤና ችግር ላይ ያሉ ወገኖችን የሚያግዙ ሊሆኑ ይገባል።

በተጨማሪም ምርምሮቹ አቅም ግንባታ ላይ የሚያተኩሩ በመሆናቸው በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ የጠየቁት ሚኒስትር ዴኤታዋ የትብብር ማዕቀፎቹን ወደ ስራ ለማስገባት በተቋማቸው በኩል ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

የልኡካን ቡድኑ አባላት በበኩላቸው በተፈረመው ስምምነት መሰረት ፕሮጅክቶችን እንደሚደግፉ መግለጻቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *