ዘመናዊ የመስኖ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል :- ኢንጂነር በየነ በላቸው

ኢንጂነር በየነ በላቸው
Spread the love

ዘመናዊ የመስኖ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል::

ኢንጂነር በየነ በላቸው

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመስኖ ልማትና አስተዳደር ኤጄንሲ በመስኖ ተቋማት አስተዳደርና አጠቃቀም ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በካፋ ዞን ግምቦ ወረዳ እየሰጠ ይገኛል።

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የክልሉ የውሃ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው ዘመናዊ የመስኖ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻል በመሆኑ ተግባሩ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተናግሯል።

የመስኖ ውሃ ተጠቃሚ ማህበራት አቅማቸውን በማጎልበት በክልሉ መንግሥት ከፊተኛው ሀብት የሚወጣባቸውን የመስኖ አውታሮችን በሙሉ አቅም ወደ ልማት በማስገባት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በክልሉ በጥቅሉ 82 የመስኖ አውታሮች የተገነቡ ሲሆን ከዚህም ውስጥ በቁጥር 57 የሚሆኑት አሁን ላይ የተሟላ ግልጋሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ነው በመድረኩ የተገለጸው።

የክልሉ መንግሥት የአርሶና አርብቶአደሮችን ህይወት በዘላቂነት ለማሻሻልና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በመስኖ አውታር ግንባታ እና የውሃ መሳቢያ ፓምፕ እያቀረበ መሆኑም ተመላክቷል።

በተቋም አስተዳደር ና የማህበራት ተግባር ላይ የሚሰጠው ስልጠና በመስኖ አውታሮች አስተዳደርና አጠቃቀም ላይ ያላቸውን ግንዛቤ እንደሚያሳድግላቸው ያነጋገርናቸው የስልጠናው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

የዘርፉን ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም ተጠቃሚ ማህበራት ግንዛቤ በማሳደግ የመስኖ አውታሮችን በዘላቂ ወደ ልማት ለማሳገድ ያለመው ስልጠናው ለተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ ነው የተገለጸው።

በመድረኩ የክልል ባለድርሻ አካላት፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም መስኖ ተጠቃሚ ማህበራዊ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *