“ሚዛን ትራክተር” በሚዛን አማን ከተማ ተገጣጥሞ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለማሰራጨት ስራ መጀመሩ ተገለጸ።

Spread the love

ስያሜውን በሚዛን ከተማ ስም ያደረገው “ሚዛን ትራክተር” በከተማችን ተገጣጥም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለማሰራጨት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቆ ወደ ስራ መገባቱ ተገልጿል።

ዳግም ኬኔዲ ጠቅላላ ንግድ ስራ ድርጅት ከግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ያለመውን ኘሮጀክት ከሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የተረከበው 4 ሄክታር መሬት ላይ ስራውን ለመጀመር ታህሳስ 12/2016 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል ይፋ አድርጓል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ እንደገለፁት አሁን ላይ ሀገራችን በግብርና ዘርፉ የጀመረችውን መነቃቃት በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በተለይም “ሚዛን ትራክተር” የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መገጣጠሙ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የትራክተር እጥረትን የሚያስቀር በመሆኑ ልዩ እድልም ነው ብለዋል።

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም በበኩላቸው ትራክተሩ ህብረብሔራዊት ከተማ በሆንችሁ ሚዛን አማን ላይ መገጣጠሙ ደስ ብሎናል ብለዋል።

ዳግም ኬኔዲ ጠቅላላ ንግድ ስራ ድርጅት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከተመሠረተበት 2004 ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ኢንቨስትመንት ባቋቋመው ዘመናዊ የማሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ እየሰራ የሚገኝ ሀገር በቀል ተቋም ሲሆን ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ፣ የሀይል አቅርቦትን በማሳደግ ፣ ግብርናውን በማዘመን እንዲሁም የግንባታ ግብዓትን በሀገር ውስጥ በሟሟላት በኩል ከፍተኛ አስተዋፅአ እያበረከተ ይገኛል።

ድርጅቱ በከተማችን በከፍተኛ ካፒታል ግዙፍ የትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ ግንባታ ማስጀመር ላይ ይገኛል።

ይህ የትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ ላለፉት አምስት አመታት በዘርፉ ጥናት በማድረግ የተቋቋመ ሲሆን የኢትዮጵያ መልካምድርን ታሳቢ ተደርገው የሚገጠሙት ትራክተሮች ኢትዮጵያዊ ስያሜ ያላቸው እና የመለዋወጫ እቃዎች ግብአት ከነባለሙያው በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ በአካባቢው እንዲያገኝ የሚያደርግ መሆኑ ተጠቁሟል።

ዳግም ኬኔዲ ጠቅላላ ንግድ ስራ ድርጅት “ሚዛን “በሚል ስያሜ የሚገጣጥማቸው ትራክተሮች ለአርሶአደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ እና የብድር አማራጭ ለማቅረብ ከግሎባል ኢትዮጵያ ባንክ ጋር በጥምረት በመስራት ላይ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል።

በተጨማሪም « ሚዛን » በሚል የከተማው ስያሜ የተሰጠው ትራክተር እንዲሁም ጄኔሬተር እና ፓምኘ ገበያ ላይ ለማስተዋወቅ በፊልም ስራዎቹ እና በቴሌቪዥን ኘሮግራም አቅራቢነት እንዲሁም የማስታወቂያ ባለሙያ የሆነው ሁሉገብ አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ለቀጣዮቹ 12 ወራቶች ለመስራት ባሳለፍነው ማክሰኞ ታህሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ስምምነት ላይ በመድረስ የድርጅቱ ብራንድ አምባሳደር ሆኖ መሾሙን የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *