ፀጋዎቻችንን ወደ ተጨባጭ ኃብት በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን የመገንባት ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

Spread the love

ፀጋዎቻችንን ወደ ተጨባጭ ኃብት በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን የመገንባት ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ መርቀው ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በብዙ ፀጋዎች የታደለች አገር ናት፤ ለዚህም የኮንታ ዞን የታደለው የተፈጥሮ ፀጋ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሦስት ነገሮችን አጥብቀን መሻትና ማስተዋል ይገባናል ነው ያሉት።

እነዚህም የማየት፣ የመሥራት እና ጠብቆ የማስቀጠል ብልጽግናዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

የማየት ብልጽግና የሚባለው ፊት ለፊት የሚታየውን ነገር በአግባቡ መመልከትና የተሻለ ዕድል መኖሩን ማስተዋል መሆኑን ተናግረዋል።

የማየት ብልጽግናን ያልታደለ ሰው በአጠገቡ ያለው ኃብት ዕዳ ሊሆንበት ይችላል ብለዋል።

የተሰጡንን ፀጋዎች ማየት ካልቻልን ሌሎች ማየት የሚችሉ ሊወስዱብን እንደሚችሉም ነው የጠቆሙት።

ብዙዎች የማየት ብልጽግና ባለመታደላቸው ኃብት ላይ ተቀምጠው ኃብታቸውን ሌሎች ሲውስዱባቸው እንደሚስተዋል አንስተዋል።

በመሆኑም ፀጋዎቻችንን በሚገባ ማየት ያስፈልገናል ብለዋል።

የማየት ብልጽግና ብቻውን ውጤት እንደማያመጣ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመሥራት ብልጽግና መከተል እንዳለበት ተናግረዋል።

ኃብት በሥራ ካልተገለጠ ዋጋ ስለማይኖረው ከማየት በኋላ ተግቶ መሥራት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህ ደግሞ እጅን ከሌብነት፣ ልብን ከክፋት ማፅዳት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ከማየትና ከመሥራት ብልጽግና በኋላ ደግሞ የመጠበቅና የማስቀጠል ብልጽግና አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በአንድ በኩል ታሪክን መጠበቅና ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በሌላ በኩል ጎብኚዎች ከሚጠሏቸው ነገሮች እራስን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

ጎብኚዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ደግነት፣ እንግዳ ተቀባይነትና ተባባሪነት እንደሚወዱ ገልጸው፤ በሰላም እጦት ምክንያት ኢትዮጵያን በብቃት ለማየት እንደሚቸገሩ ጠቁመዋል።

በመሆኑም የማያግባቡን ነገሮች ቢኖሩም እኛንና ሀገራችንን ለማየት ለሚመጡ ጎብኚዎች ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ይህ ደግሞ የፖሊስ ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ነው በመግለጽ።

ጎብኚዎች ሌላው የሚጠሉት ነገር ሌብነትና ልመና መሆኑን በመጥቀስ፤ ሀገርን በመጥፎ ከሚያስጠሩ ነገሮች መቆጠብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የማየት፣ የመሥራትና ጠብቆ የማስቀጠል ብልጽግና ላይ በማተኮር ፀጋዎቻችንን ወደ ተጨባጭ ኃብት በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን የመገንባት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *