



”ትውልድ በመምህራን ይቀረጻል፣ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሁሉም አከባቢ ከተወጣጡ ከትምህርት ቤት አመራሮች እና መምህራን ጋር የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
የትምህርት ቤት አመራሮች እና መምህራን ከውይይት መድረኩ ጎን ለጎን በርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት እና በርዕሰ መስተዳድር ዶክተር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ቅርብ ክትትል የተገነባዉ የቦንጋ ከተማ ኮሪደር ልማት አካል የሆነዉን የአረንጓዴ ፓርክ ጉብኝት አድርገዋል።
ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የቤንች ሸኮ ዞን የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አገኘው ወርቁ እንደገለጹት፤ በክልሉ ብዝሃ ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው ቦንጋ ከተማ የተገነባው የኮሪደር ልማት አካል የሆነዉ የአረንጓዴ ፓርክ ትውልድን ታሳብ ባደረገ መልኩ የተገነባ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር እና የከተማውን ገጽታ የሚቀይር ነዉ።
የተለያዩ የመዝናኛ እና የህጻናት መጫወቻ ሥፍራዎችን የያዘዉ የአረንጓዴ ፓርኩ ተሞክሮ ወደ ሌሎች ክልል ከተሞች መስፋት እንደሚገባ ጠቁመው ኮሪደር ለማህበረሰቡ ምቹ አከባቢ እንዲፈጠር እያገዘ በመሆኑ በከተማም ሆነ በገጠር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት በኩል የተገነባዉ የአረንጓዴ ፓርክ ከዚህ በፊት ተሰርተው የማይታወቅ እጅግ የሚደነቅ የልማት ሥራ ነው ያሉት ደግሞ የቦንጋ ከተማ ባርታ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆነችው መምህርት ጽጌ ዮሐንስ መንግስት የጀመራቸውን ከተማዉን አረንጓዴ ማልበስ እና የማስዋብ ሥራ ህዝቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
መምህርት ጽጌ መምህራን መንግስት ጥያቄዎያቸውን አግባብነት ባለው መንገድ እንዲመልስ እየጠየቀ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በሥነ ምግባርና በግብረገብ በማነጽ የተጀመረውን የአረንጓዴ ልማት ሥራውን ማስቀጠል እንዲያስችሉ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸዉም ተናግረዋል።
የቴፒ ከተማ ቁጥር ሁለት ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ፍቅር አበበ በበኩላቸው ክልሉ ከተጀመረ ባጭር ዓመት የመፈጸም እና ማስፈጸም አቅም በመጨመር የተለያዩ እንሼቲቮችን ተግባራዊ ከሚያደርገዉ ሥራዎች መካከል የቦንጋ ከተማ ኮሪደር ልማት አካል የሆነዉ የአረንጓዴ ፓርክ ሥራ አንዱ ማሳያ ነው።
በከተሞች የተጀመሩት ከተሞችን በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ሥራ በገጠሩ አከባቢዎች እና በትምህርት ቤቶች በሀገር በቀል ውጤቶች በትኩረት መሠራት እንዳለበት ነው ርዕሰ መምህሯ የገለጹት።
በርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት አማካኝነት በከተማዉ የተገነባዉ የኮሪደር ልማት አካል የአረንጓዴ ፓርክ በየደረጃው ወደ ታች በማውረድ ህዝቡን በማነቃነቅ ሀብት በማሰባሰብ ሊሰሩ የሚገቡ እንደሆናቸውም የጠቀሱት ደግሞ የቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ የቅጤ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር መሰለ መልካሙ ናቸዉ።
የኮሪደር ልማት ሥራ በተለይም በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በማስጀመር ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑንም መምህሩ ተናግረዋል።
በፍቅር ከበደ
