የክልሉ መንግስት በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው -ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት “ትውልድ በመምህራን ይቀረጻል፣ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ ቃል ክልላዊ ማጠቃለያ የመምህራን ውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት በክልሉ የትምህርት ስብራት መጠገን፣ የትምህርት ጥራት ማሻሻል እና መምህራን የሚያነሷቸው ጥያቄዎችን መፍታት የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥተው የሚሰራባቸው ጉዳዮች መሆናቸዉን ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፉት ጊዜያት የትምህርት ስብራት ለመጠገን እና የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ነው ርዕሰ መስተዳደሩ የገለጹት።

በእነዚህ ዓመታትም ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማ ምቹ እንዲሆኑ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል፣ የትምህርት ግብዓት ማሟላት እና የመምህራን አቅም ማጎልበት ሥራዎች ትኩረት ተሰጥተው ሲሰሩ ቆይቷልም ብለዋል።

ሀገር የሚገነባው በዕዉቀትና በጥበብ ነው ይህም የሚመነጨው በመምህራን እንደሆነም ያነሱት ርዕሰ መስተዳድር መምህራን የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለመገንባት እያደረገ የሚገኘው ሥራ የበለጠ ማጠናከር አለበት ስሉም ጠቅሰዋል።

በክልሉ ባለፉት ጊዜያት በዘርፉ በተመዘገቡ ውጤቶች በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ቤት አመራሮች እና መምህራን ላበረኩት አስተዋጽኦ ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ምስጋና አቅርበዋል።

የክልሉ መንግስት መምህራን የሚያነሷቸው የተለያዩ የጥቅማጥቅም ጥያቄዎችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰራም ገልጸው የመምህራን አቅም ለማጎልበት የአጭር፣መካከለኛ እና የረዥም ጊዜ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘዉዴ ለመወያያ የተዘጋጀ ሰነድ እያቀረቡ ይገኛሉ።

በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ በክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች እና ከክልሉ ከሁሉም አካባቢዎች የተወጣጡ የትምህርት ቤት አመራሮች እና መምህራን እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *