የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?

Spread the love



ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት ‘’የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?’’ በሚል አምድ ሥር አጠቃላይ የክልላችንን ገጽታ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ የካፋ፣ የዳዉሮ፣ የቤንች ሸኮ እና የሸካ ዞኖችን አጠቃላይ ገጽታ የሚያሳዩ ጽሁፎችን እንደየቅደምተከተላቸው ለውድ አንባቢያን አጋርተናል፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ከክልላችን ዞኖች አንዱ የሆነውን የኮንታ ዞንን እንቃኛለን፡፡

መልካም ንባብ!
የኮንታ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተደራጁ ስድስት ዞኖች አንዱ ነው፡፡ ዞኑ በሦስት ወረዳዎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ ሲሆን በእነዚህም መዋቅሮች 15 የከተማ እና 47 የገጠር ቀበሌዎች በድምሩ 62 ቀበሌዎች ይገኛሉ። ዞኑ በስተ ሰሜን በኩል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በጅማ ዞን ዴዶ እና ማንቾ ወረዳዎች፣ በስተምዕራብ በኩል በከፋ ዞን ጨታ፣ ዴቻ፣ ጠሎና አዲዮ ወረዳዎች፣ በስተ ምሥራቅ በኩል በዳውሮ ዞን ታርጫ ዙሪያ፣ ቶጫ፣ ኢሰራ ወረዳዎች፤ በስተደቡብ በኩል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በደቡብ ኦሞ ዞን ሰላማጎ ወረዳ እና በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ይዋሰናል፡፡

የዞኑ ዋና ከተማ አመያ ሲሆን ከዞኑ ዋና ከተማ መነሻ አንስቶ ከአገሪቱ ርዕሰ መዲና ከአዲስ አበባ- ጂማ-አመያ 465 ኪ/ሜ፣ ከክልሉ የፖለቲካና አስተዳደር መቀመጫ ብዝሃ ከተማ ቦንጋ በ82 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
የኮንታ ዞን በ6.46′-7.26′ ሴሜን ላቲቲዩድ’’ እና በ36.32-36.87 ምስራቅ “ሎንግቲዩድ” መሥመሮች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን አጠቃላይ የዞኑ ቆዳ ስፋት 238,163 ሄክታር ሲሆን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ 28% ሜዳማ፣ 38.5% ተራራማ እና 33.5% ተዳፋታማ ነው። ዞኑ ከባህር ጠለል በላይ ያለው ከፍታ ከ790 እስከ 2,750 ሜትር ሲሆን የአየር ንብረቱም ደጋማ 6%፣ ወይና ደጋ 54% እና ቆላ 40%፤እንዲሁም አማካይ የሙቀት መጠን 25.5 ድግሪ ሴንቲግሬድ ነዉ። ዞኑ የበልግና የመኸር ዝናብ ተጠቃሚ ሲሆን ከፍተኛው የዝናብ መጠን 2,290 ሚ.ሜ እና ዝቅተኛው 1,200 ሚ.ሜ ሆኖ አማካይ የዝናብ መጠን 1,745 ሚ.ሜ ነዉ።

በዞኑ ካለው አጠቃላይ ቆዳ ስፋት 238,163 ሄክታር መሬት ላይ 22,584.76 ሄ/ር በቋሚ ሰብል፣ 76,742ሄ/ር በዓመታዊ ሰብል፤ በድምሩ 99,326.76 ሄ/ር መሬት በቋሚና ዓመታዊ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን ሽፋኑም 58.4% ነው፡፡ በተፈጥሮ ደን 94,766.34 ሄ/ር፣ በማህበራት 1,300.5 ሄ/ር፣ የግል ደን 2,384.25 ሄ/ር ለግጦሽ የተከለለ መሬት 4,141 ሄ/ር፣ወደፊት ሊለማ የሚችል 14,068.99 ሄ/ር ወደፊት ሊለማ የማይችል 462 ሄ/ር አጠቃላይ በደን የተሸፈነ የመሬት ክፍል በሄ/ር 107,450.09 ሲሆን ሽፋኑ 46.1% ነው፡፡ አጠቃላይ የለማ 225,190.4 (94.5%) ሄ/ር መሬት ነው፡፡ በግንባታ የተከለለ 3,991 ሄ/ር፣በቁጥቋጦ የተሸፈነ 16,115.7 ሄ/ር፣በውሃ የተሸፈነ 1,072 ሄ/ር፣በቦረቦር የተያዘ መሬት 217.3 ሄ/ር እና በረግረግ የተሸፈነ መሬት 317.16 ሄ/ር ነው።

የዞኑ ነባር ብሔረሰብ ኮንታ ሲሆን ቋንቋውም ኮንቲኛ ሲባል በኦሞአዊ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ በተጨማሪም በዞኑ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ከነባሩ ብሔረሰብ ጋር ተጋብተው፣ ተዋልደው፣ ተከባብረውና ተስማምተው በጋራ የሚኖሩበት ነው፡፡ የዳዉሮ፣ የካፋ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ እና ሌሎችም ብሔረሰብ አባላት ከረዥም ጊዜ አንስቶ ከነባሩ ብሔረሰብ ጋር በሠላምና በፍቅር ይኖራሉ፡፡ መንግስት የገጠር ማህበረሰብን የምግብ ዋስትና ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በነደፈዉ የሰፈራ ፕሮግራም ከወላይታ እና ከሀዲያ ዞኖች የመጡ የወላይታ እና ሀዲያ ብሔረሰብ ተወላጆች በዞኑ በኮንታ ኮይሻ ወረዳ ወስጥ ሰፍረዉ ይገኛሉ፡፡ ይህም ዞኑ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እና አብሮ ተቻችሎ የሚኖሩበት ትንሹ ኢትዮጵያ ያደርገዋል፡፡

የኮንታ ህዝብ መተዳደሪያና የገቢ ምንጭ በዋናነት ጥምር ግብርና ሲሆን የንግድና ሌሎች የዕደ ጥበብ ስራዎችም አንዱ አካል ነው፡፡

ዞኑ በሰብል ልማት ምርት፡-
የሰብል ልማት በዞኑ በእርሻ ልማት ዘርፍ የምግብ ዋስትናን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ የኤክስፖርት ምርቶችን ለማሳደግና የኢንዱስትሪ ግብዓት ፍላጎትን ለማሟላት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ በዋናነት በአነስተኛ አርሶ አደር ማሳ ላይ የሚያተኩር ሆኖ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ሰፊ ትኩረት በመስጠት የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ እንዲጨምር ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት የሰብል ልማት ሥራዎችን በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች በመክፈል ለኢንቨስተሮች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግንዛቤ በማስጨበጥ ቀጣይ የግሉ ዘርፍ በሰፊው እንዲሳተፍ የዞኑ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በቅባት ሰብሎች
የቅባት እህሎች በአብዛኛው ጊዜ ለአገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ እንደመሆናቸው መጠን ኢንቨስተሮች ቢሳተፉ ተጠቅመው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የድርሻቸውን አሻራ የሚያሳርፉበት ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በዞኑ የሚመረቱ የቅባት ሰብሎች አማካይ የምርት መጠን በሄክታር ሰሊጥ 8.1 እና ለዉዝ 8 ኩ/ል ማምረት የሚያስችል የአየር ንብረትና ከ4,382 ሄ/ር በላይ የመሬት ዝግጅት በዞኑ መንግስት በኩል የተጠናቀቀ በመሆኑ በልማቱ ለመሳተፍ የሚመጣ ባለሀብት ያለ አንዳች እንከን ውጤታማ እንደሚሆን ዞኑ ከተለያዩ የምርምር ማዕከላት ጋር በዘርፉ የተደረገ ሰርቶ ማሳያ አማካይ ውጤት ምስክር ነው፡፡

በጥራጥሬ ሰብሎች
የጥራጥሬ ልማት በዞኑ የበልግና መኸር ምርት ወቅትን ጠብቆ እየለማ ያለ ሲሆን የሚመረቱትም ቦሎቄ፣ባቄላ፣ማሾና አተር ናቸው፡፡

በብዕር ሰብሎች
በዞኑ የብዕር ሰብል ተብለው የሚመረቱ በዋናነት ጤፍ ፣ ስንዴ ፣ ገብስና ሩዝ ሲሆን በመሰረታዊ የዕድገት አማራጭ በመጠቀም ዞኑ በሁሉም በአማካይ ጤፍ 18፣ስንዴ 54፣ ገብስ 22፣ ሩዝ 43 ኩ/ል ምርት በሄ/ር በበልግና መኸር የምርት ወቅት ማምረት የሚቻል በመሆኑ ባለሀብቶች በመረጡት የሰብል ልማት ዘርፍ እንዲሳተፉ እንዲሁም በድህረ-ምርት ወቅት እንደ ሀገርም ይሁን እንደ ዞን እያጋጠመ ያለውን የምርት ብክለትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የአማካይ ምርት መጠን በሄክታር ከፍ ማድረግ የሚቻል በመሆኑ ዞኑ ከ15,212 ሄ/ር በላይ ለብዕር ሰብል ልማት የመሬት ዝግጅት በማድረግ ለኢንቨስተሮች በሩን ክፍት አድርጎ እየጠበቀ ይገኛል፡፡

በአገዳ ሰብሎች
ዞኑ ዋነኛ የበልግና መኸር ወቅት ልማት በቆላማ ቀበሌዎች የሚያተኩረው በአገዳ ሰብሎች ምርት ላይ ቢሆንም በወይና ደጋና ከፊል ደጋማ በሆኑ በመዋቅሮች በስፋት እየተመረተ ይገኛል፡፡ በዚህም የተለያዩ ሰርቶ ማሳያ ሥራዎች ከምርምር ማዕከላት ጋር በጋራ ተካሂደው በተገኘና አርሶ አደሮች እያመረቱ ካሉት ከ10 ሺህ በላይ ምርት በማምረት ተጨባጭ ምርት ቅመራ የተገኘ አማካይ የምርታማነት መጠን በሄክታር በቆሎ 80-108 ኩ/ል ምርት መሰብሰብ እንደሚቻል በተግባር ተሞክሮ የታዬ ነው ፡፡ ስለሆነም በዘርፉ ለሚሰተፉ የግል ባለሀብቶች የዞኑን ሥነ-ምህዳር ያገናዘበና ለዚሁ ልማት አመች በሆኑ መዋቅሮች 13,544 ሄ/ር መሬት አዘጋጅቶ እየጠበቀ ይገኛል፡፡
የእንስሳትና ዓሳ ሀብትልማት
ለዞኑ አርሶ አደሮች እንዲሁም ለከተማ ነዋሪዎች አንፃራዊ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የላቀ ነዉ፡፡ በተጨማሪ ዞኑ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ክምችት ያለው ሲሆን አብዛኛው ህ/ሰብም በዚህ ዘርፍ የሚሳተፍና በዘርፉ የካበተ ልምድ ያለ መሆኑና ለዘርፉ ተፈጥሮ የለገሰው ምቹ ሁኔታ መኖሩ ከፍተኛ ዕድል ነው። በመሆኑም ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተገነቡ ተቋማዊ አቅሞችን፣ በመጠቀም ለተቋሙ ከተሰጠዉ ልዩ ትኩረት የተሠሩ ዋና ዋና ተግባራትና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር ለማስፋት በሚያስችል አግባብ በዘርፉ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ፡፡
የእንስሳት ሀብት መረጃ እንደሚያሳየዉ
ዳልጋ ከብት ብዛት 290,314 አነስተኛ አመንዣክ በግ ብዛት 99,692
ፍየል ብዛት 70,769፣ዶሮ ብዛት 345,225
የጋማ ከብት ብዛት 20,171፣ የንብ ቤተሰብ በዛት 193,455 ይገኛል፡፡

በዚህም መሠረት ዞኑ በእንስሳት ዘርፍ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ገቢ ለአርሶ አደሩና በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያስገኝና በማር ምርት እምቅ አቅምና በዘመናዊና በባህላዊ አረባብ ተፈጥሮ የለገሰ ምቹ አቅም ያለዉና በዓሳ ሀብት ልማት 6 ዋናዋና ሐይቆችና ሁለት ትላልቅ ወንዞች ማለትም ሾሽማና ጎጆብ ወንዝ ዉስጥ አንባዛና ቆሮሶ እንዲሁም የተለያዩ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡በተጨማሪም ወደ 8 የሚጠጋ ዘመናዊ ጋንዳ ተዘጋጅቶ የዓሳ ጫጩት በማልማት ለራሱ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥና ለገበያ በማቅረብ አየተጠቀመ ይገኛል፡፡

በሥጋ ሀብት ልማት በማድለብ አርሶአደሩ ገበያን በመከተል በሬንና ላምን 2ዙር ለአከባቢና ለማዕከላዊ ገበያ ከጪዳና አመያ በሳምንት ከ15—20 መኪና እየተጫነ ነዉ ፡፡
በማሞከት በግና ፍየልን በአጭር ጊዜ አርሶአደሩ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እዲላቀቅና የገቢ መጠኑ በመጨመር በዓመት 4/አራት /ጊዜ ለአካባቢና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ከአመያና ጪዳ ገበያ ቢያንስ በአንድ ሳምንት ዉስጥ ከ30-40 መኪና በመጫን ለማዕከላዊ ገበያ ጭምር በማቅረብ ላይ ሲሆን በዚህ ዘርፍ የሚሰማራ ባለሀብት ተጠቃሚ ይሆናል ፡፡

በማር ምርት አሁን ባለዉ ነባራዊ ሁኔታ የተለያዩ ማር አርሶ አደሩ በማምረት ከባህላዊና ዘመናዊ ቀፎ የሚመረት የተፈጥሮ ማር ለመድኃኒት የሚሆን በገበያ በጣም ተፈላጊና በአጭር ጊዜ ለጥቅም የሚደርስ ምቹና ተስማሚ የአየር ጠባይ የሚገኝ ነዉ ፡፡
ከዶሮ ሀብት ልማት ጋር በተለይ የ1ቀን ዕድሜ ጫጩት ለ45 ቀን ብቻ በማሳደግ ለወጣቱና ለሴቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ምቹና ተስማሚ አካባቢ ስለሆነ በዘርፉ የሚሳተፉ ባለሀብትና ወጣቱ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡እንዲሁም የእንቁላልና ሥጋ ምርት ዶሮ አሳድጎ ለመጠቀም ምቹ የሆነ የሥራ ቦታ አለ፡፡
በአጠቃላይ ዞኑ እምቅ የተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ አቅም ያለዉ በመሆኑ በዘርፍ የሚሠማራ ወጣትና ባለሀብት ለራሱም ሆነ ለአከባቢዉ የሚጠቅምና በአጭር ጊዜ ዉጤት በማምጣት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችል በቂ ባለሙያ በተለያየ ዘርፍ የሙያዊ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ የተዘጋጀ የባለሙያ አቅም ያለበት አካባቢ ነው።

👉የፍራፍሬ ምርት
ዞኑ ለፍራፍሬ ሰብል ተስማሚ የአየር ፀባይ እና ሥነ-ምህዳር፣ሰፊ መሬት ፣በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያና ማልማት የሚችል ልምድ ያለ አርሶ አደር መኖሩ በፍራፍሬ ልማት ሥራ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያደርግ ሲሆን በተጨማሪም እንዴ ዞን ተጨባጭ ሁኔታ ሊለማ የሚችል በቂ ከ28 ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት እንዳለ የተረጋገጠበት ሲሆን ከዚህ ዉስጥ ከ8 ሺህ ሄ/ር በላይ የለማ በመሆኑ ቀሪ በስፋት ማልማት የሚያስችል አቅም መኖሩን ያረጋግጣል ፡፡
ሌላዉ ዘርፉ መጠነ ሰፊ ጥቅም እያስገኘና ከዚህ መነሻ በአ/አደሩ ዘንድ ሰፊ አመኔታ ያስገኘበት እና የሁሉንም ቀልብ የሳቤ በመሆኑ ከአካባቢም ሆነ ከአካባቢ ዉጭ የሚመጣዉ ኢንቨስተር ወደ ዞኑ በመምጣት የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆን ለራስም ሆነ ለአከባቢ ማሕበረሰብ ከሚሰጠዉ አገልግሎት በላይ ለሀገር የሚያመጣዉ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ታዉቆ ተጠቃሚ ለመሆን እየተሰራ ይገኛል፡፡

ከጤና ተቋማት አንፃር በዞኑ 1 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ 4 የመንግስት ጤና ጣቢያዎች፣ 55 ጤና ኬላዎች፣ 15 የግል ክሊኒክ፣ 10 የግል ፋርማሲ እና 1 የማህበረሰብ ፋርማሲን ጨምሮ በአጠቃላይ 86 የመንግስት እና የግል ጤና ተቋማት ይገኛሉ።

ከትምህርት ተቋማት አኳያ በዞኑ 58 ቅድመ መደበኛ፣ 57 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 7 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 1 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እና 7 የግል አፀደ ህፃናት ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ።

ዞኑ በተለያዩ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች የታደለ ሲሆን ከባህላዊ ሀብቶች አንፃር የብሔረሰቡ ዘመን መለወጫ ስርዓት ህንግጫ (Hingicaa)፣ አባቶች በቀደሙት ዘመናት ከአጎራባች አካባቢዎች ወረራ የብሔረሰቡን ድንበር ለማስጠበቅ የቆፈራቸዉና ዞኑን እንደመቀነት የዞረ ጉድጓድ ቦሁዋ (Boohuwa)፣ ከአፈር ብረት የሚመረትበት ባህላዊ አሰራር፤ በሀዘንና በደስታ ጊዜ የሚገለገሉባቸዉ መገለጫዎች እንደ ለቅሶ፤ ሰርግ፣ ጭፈራ ስነ-ስርዓቶች፣ ባህላዊ የመዚቃ መሳሪያዎች፣ ምግቦችና መጠጦች የሚጠቀሱ ሲሆን ከተፈጥሯዊ ሀብት አንፃር የጨበራ ጩረጩራ ብሔራዊ ፓርክና በዉስጡ የሚገኙ የተለያዩ የእንስሳትና አዕዋፍ ዝሪያዎች፤ ለመጠጥና ለመድሃኒት አገልግሎት የሚዉሉ ፍል ዉሃዎች፤ ፏፏቴዎች፣ ዋሻዎች፣ ሀይቆች፣ የተፈጥሮ ማዕድናት እንደ ድንጋይ ከሰልና የብረት ማዕድን፣ ጥቅጥቅ ያሉ ጥብቅ የተፈጥሮ ደንና የጫካ ቡና በከፊል የሚገለፁ ናቸዉ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነባው የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ እና ከኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ግዙፉ የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብም በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ሀብቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በዞኑ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶችም ሲገኙ በ1882 ዓ.ም የተመሰረተው የአጋሬ ቅዱስ ሚካኤልና የገንጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተክርስቲያናት ይጠቀሳሉ።

በአሁኑ ሰዓት ዞኑ ካለው እምቅ የተፈጥሮ አቅም የተነሳ በርካታ የሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ማረፊያ እየሆነ መጥቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *