ለፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ በሚመደቡ ሀብቶች ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ተደማሪ ሀብት ለማግኘት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ

Spread the love

ክልላዊ የልማት ክፍተቶችን ለመቅረፍ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚመጡ ሀብቶችን ከዓለም ባንክ ጋር በተገባው ስምምነት መሰረት በተገቢው ስራ ላይ ማዋል እንደሚጠበቅም ተገልጿል ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፋይናንስ ቢሮ የካልም ፕሮጀክት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተደርጓል ፡፡

በአፈጻጸም ግምገማው የተገኙት በክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የመንግስታት ትብብር ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ዓለሙ ለፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ በሚመደቡ ሀብቶች ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ተደማሪ ሀብት ለማግኘት ትኩረት በመስጠት መስራት ይገባል ብለዋል ፡፡

ፕሮግራሙ ውጤታማ እንዲሆን ለሚመለከታቸዉ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠቱንና ተግባሩን ውጤታማ ለማድረግ እንዲያስችል በቁሳቁስ የመደገፍ ስራዎች መሰራታቸውን አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል ፡፡

በዚህም በካልም ፕሮግራም በ2016 በጀት ዓመት 46 ኮምፒውተሮችና ጀነሬተሮችን ለዞንና ወረዳዎች ድጋፍ መደረጉንና በዚህም በጀት ዓመት ተጨማሪ 46 ኮምፒውተሮችን ተግባሩን ውቴታማ ለማድረግ ድጋፍ ተደርጓል ፡፡

በካልም ፕሮጀክት ተጠቃሚ ወረዳዎች ተገቢውን ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለፕሮግራሙ ውጤታማነት የሚወርዱ ቁሳቁሶች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ መደረግ ይገባዋልም ብለዋል፡

በበጀት ዓመቱ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ በካልም ፕሮግራም የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየቱንም አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል ፡፡

በክልሉ ፋይናንስ ቢሮ የቻናል አንድ ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ጌታሁን ታደሰ በካልም ፕሮግራም የተከናወኑ ፋይናንሺያል ሪፖርት አቅርበዋል ፡፡

የካልም ፕሮግራም ከ2012 በጀት ዓ/ም ጀምሮ ወደ ስራ የገባ መሆኑን ያወሱት አቶ ጌታሁን በክልሉ አሁን ላይ በ40 ወረዳዎች በተፋሰስ ልማት ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ለ40 ወረዳዎች 272 ሚሊዮን 766 ሺህ 559 ብር ጸድቆ በኑሮ ማሻሻያ፣ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለተፋሰስ ልማት ማህበራት ወርዶ ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል፡፡

ወረዳዎች በፕሮግራም በጀት አፈጻጸማቸው ያሉበትን ደረጃ ዳሰሰ ሪፖርት ያቀረቡት አቶ ጌታሁን ፕሮግራሙ ውጤታማ እንዲሆን በክፍተት የተለዩ ችግሮችን ፈጥኖ ማረምና ማስተካከል ከሁሉም የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ወረዳዎችና ዞኖች የሚጠበቅ መሆኑንም አስታውቀዋል ፡፡

በሌላ በኩልም በክልሉ በዩኒሼፍ ፕሮግራም የሚደገፉ ወረዳዎች አፈጻጸማቸው ያሉበትን ደረጃ የሚዳስስ ሪፖርት በክልሉ ፋይናንስ ቢሮ የዩኒሴፍ ፕሮግራም አስተባባሪ በሆኑት በአቶ አጼ ቴዎድሮስ ቀርቧል ፡፡

በዩኒሴፍ ፕሮግራም ለታቀፉ 17 መዋቅሮች የፋይናንስ ሂሳብ አመዘጋገቦችን ለማሳለጥ እንዲያስችል ለአይቤክስ ምዝገባ 17 ኮምፒውተሮች ተገዝተው መሰራጨታቸውን አቶ አጼ ገልጸዋል ፡፡

በቀረቡ አፈጻጸም ሪፖርቶች ላይ ተሳታፊዎች አስተያየትና ጥያቄዎችን በማንሳት ከሚመለከታቸውና ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት መድረኩ ተጠናቅቋል፡፡

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *