




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና ሰዉ ሀብት ልማት ቢሮ በሪፎርም የሚካተቱ የክልል ቢሮዎች፣ ለዞን መምሪያ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲና በክልሉ ፍኖተ ካርታ ላይ የተዘጋጀ ስልጠና በቦንጋ ከተማ እተሰጠ ይገኛል፡፡
የቢሮዉ ሃላፊ አቶ አስራት አዳሮ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸዉ፣የመንግስት የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ትግበራ ዓላማ የመንግስት ተቋማትን ቅልጥፍናና ዉጤታማነት፣ግልጽነት፣እና ተጠያቂነት በማሻሻል ቀልጣፋ ዉጤታማ አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን ፍላጎት ማሟላት መሆኑን እና ቢሮዉ ለሪፎርም ስራ ተግባራዊነት እና መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚስችሉ ተግባራት ላይ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል በነበረዉ አሰራር ስርዓት እጅግ ብዙ መዋቅር፣መደብና የሰዉ ሃይል ካለን አገልግሎት ጋር አመጣጥነን በማደራጀት ወደ ስራ እንድንገባ የክልሉ መንግስት ባስቀመጠዉ አቅጣጫና ድጋፍ በየደረጃዉ ባሉት ተቋማት ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰዉ አሁን ያለዉን የሪፎርም ተግባራትን በተሻለ መልኩ ለማሳለጥ እንዲቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ተሰማ የስራ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፣መንግስት ፍትሀዊ እና ዉጤታማ የአገልግሎት አሰጣጥ ለመዘርጋት የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ እና በዚህም ዉጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል፡፡
በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፍኖተ ካርታ የህግ ማዕቀፎች ላይ የተዘጋጀዉ ስልጠና በአፈጻጸም ወቅት የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችን ለመሙላት የሚረዳ እንደሆነ በመግለጽ ለተግባራዊነቱም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸዉን ሃላፊነት እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡
በመድረኩም የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ፍኖተ ካርታ እየቀረበ ይገኛል።
በካሳሁን አሰፋ
