




እንደምን ቆያችሁን ውድ አምባቢዎቻችን? ባለፉት ተከታታይ ወራት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ? በሚል አምዳችን የዞኖቻችንን ጠቀለል ያለ እይታ በወፍ በረር ማስቃኘታችን ይታወቃል።
ከእነዚህም: ስለ ካፋ ዞን ባስቃኘናችሁ ክፍል: በካፋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ተፈጥሮአዊና የቱሪስት በዳረሻዎችን እንድሁም በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ነባር ብሔረሰቦች ውስጥ አንዱ የሆነውን ካፈቾ የሚታወቁባቸውን ባህላዊ እሴቶች ጠቅሰናችሁ ነበር። ዛሬ ደግሞ ከነዚህ ባህላዊ ትውፊቶች ውስጥ አንዱን መርጠን ለማስቃኘት እነሆ እንላለን።
ካፈቾ ማህበረሰብ በተለያዩ የክዋኔና ትውፊቶች ማለትም በዘፈን፣ በሠርግ፣ በለቅሶ፣ ወዘተ የሚታወቅ ሲሆን በእያንዳንዱ ዘርፎች ባህላዊና ታሪካዊ ትርጉሞች/ምክንያቶች የተጣመሩ መሆናቸው ይጠቀሳል።
ለአብነት ዘፈንን በካፈቾ ዘንድ ስንመለከት፦ለተለያዩ ኩነቶች እና ክስተቶች ይዘፈናሉ፤ አብዛኛዎችም ከሚመለከታቸው አውድ ውጭ ፈፅሞ ሊዘፈኑም አይችሉም። ከዛም ባሻገር ዘፈን አቅራቢዎችንም፦ በሴቶች ብቻ የሚዘፈኑ(ዱሞ፣ጎሞ)፣ በወንዶች ብቻ የሚዘፈኑ(ህቾ፣ግራሮ) እያሉ ከነምክያታቸው ያስቀምጧቸዋል።
የካፈቾ ሴቶች በተለያዩ አውዶች የተለያዩ ይዘት ያላቸውን ዘፈን፦ ልጅ ሲያባብሉ፣ አውድማ ሲያፀዱ፣ እህል ሲወቅጡ ወዘተ በየመልዕክቶቻቸው የሚዘፍኑ ሲሆን ለየት ላለ ክስተትም በቡድን ሆኖ ከሚከወኑት ባህላዊ እሴቶች(ዘፈኖች) ውስጥ አንዱ “ዱሞ” ነው፡፡
ዱሞ/የምልጀ ዘፈን / እንደማንኛዉም ዘፈን በተገኘበት ቦታ በዘፈቀደ አይዘፈንም፡፡ ዱሞ ከባህላዊ እምነት ጋር የተያያዘና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ባህላዊ የምልጃ ዘፈን ነው፡፡
በዚህም መሰረት በአካባቢም ይሁን ከአካባቢ ራቅ ብሎ ከመደበኛ ውጪ ወይም ያልተለመደ አዲስ ክስተት ተፈጥሮ ሲታይ ወይም ሲሰማ “ዱሞ” ይዘፈናል፡፡ ይህም ማለት ለምሳሌ ሰው ሁለት ዓይን ይዞ መወለድ ሲገባው ከዚህ ውጪ ሶስት ወይም ከዚያ በላይ እና በታች: ሌሎች አካላት እንዲሁም የዱር እንስሳትም ተፈጥሮን የሚቃረን ነገር ሲወልዱ ሊሆን ይችላል፡፡
እነዚህን እና መሰል አዲስ ክስተት ያየች ወይም የሰማች ሴት እንዳልሰማ ሆና በውስጧ ይዛው ማደር የለባትም፡፡ ምክንያቱም የተፈጠረው ነገር ደጋግሞ ይፈጠራል ተብሎ ስለሚታመን፡፡ በዚህ መሰረት: ያንን አዲስ ክስተት ያየች ወይም የሰማች ሴት ወዲያውኑ አንድ፣ ሁለት.. እያለች ለጎረቤቶቿ ትናገራለች፡፡
ከጎረቤቶቿም ጋር ይህ የታየው/ የተሰማው አዲስ ክስተት ዳግም ላለመስማት “ዱሞ ዱባ በሸበ” ይህ የሰማነውን ነገር እንደይደገም ዱሞ በመዝፈን እናሳልፈው በማለት የዘፈን ቀን ይወስናሉ፡፡
በውላቸውም መሰረት ከየትኛውም ንክክ ነፃ ሆነው (ንጽህናቸውን ጠብቀው በማደር :እሳት /ውሃ/ እንኳ በእጃቸው መንካት እንደሌለባቸው ያውቃሉና) በንጽህና አድረው በመውጣት ከየደጆቻቸው የመድሐኒትነት ባህሪይ ያላቸውን እጽዋት ማለትም እንደጤና አዳም፣ ግራዋ፣.. ወዘተ ቅጠላ ቅጠል በመሰብሰብ የኮባ ቅጠል በመልበስ በቁጥር አነስተኛ ሴቶች ዘፈን ይጀምራሉ፡፡ እንዲህም እያሉ፦
Wooha illilla wooha illila/ ዎሃ ኢሊላ..ዎሃ ኢሊላ… /ምን ሰማን አይስማ ጆሮ፣/
Wooha illilla wooha illila/ ዎሃ ኢሊላ..ዎሃ ኢሊላ… /ምን ሰማን አይስማ ጆሮ፣/
Ta genneene gondoo shoobe/ ታገነነ ጎንዶ ሾበ…/ እምዬ ከዚሁ ክፉ ነገር አማልጅን፣/
Ta genneene gondoo shoobe/ታገነነ ጎንዶ ሾቤ… እምዬ ከዚሁ ክፉ ነገር አማልጅን/
እያሉ ሲዘፍኑ ሌሎች ጎረቤቶች ይሰማሉ፡፡ ይህንን የዘፈን ድምጽ የሰሙ ሴቶች በምንም ዓይነት ዘፈኑን ከመሳተፍ ውጪ አይሆኑም፡፡ እየሰሙ ቢቀሩ ነገሩ በእነርሱ ላይ ይከሰታል ተብሎ ስለሚሰጋ ወዲያውኑ ቀዳሚ ሴቶች ያደረጉትን ሁሉ በመያዝ ቀርበው ከዘፈኑ ይቀላቀላሉ፡፡ አሁን የዘፋኞች ቁጥር እየጨመረ..እየጨመረ ይሄዳል፡፡
ምናልባት በህመም ወይም በልዩ ችግር ምክንያት እስከ ወንዙ መውረድ የማትችል ከሆነ ሰብስባ ያመጣችውን መደሃኒትና ቅጠላቅጠል አደራ አድርሱልኝ በማለት ሰጥታ በማስፈቀድ ምህረት ለምና ወደ ቤቷ ትመለሳለች፡፡
ባህላዊ ዘፈን እየዘፈኑ እያሉ መንገድ የሚሄድ ማንኛውም ሰው/ፈረሰኛም ቢሆን ከፈረስ ወርዶ ልክ ታቦት እንደመሳለም ጎንበስ በማለት ምህረት መጠየቅ አለበት፡፡ምናልባት አውቆም ይሁን ሳያውቅ ጥሶ ቢሄድ ዘፋኞቹ፣
Colloocho hammaaye callete neena/ ጮሎቾ ሃማዬ ጫለቴ ኔና…. /አንተ ጉልበተኛ ንቀህ አትሂድ አውግዤሃለሁ፣/
Colloocho hammaaye callete neena/ ጮሎቾ ሃማዬ ጫለቴ ኔና… /አንተ ጉልበተኛ ንቀህ አትሂድ አውግዤሃለሁ፣/
በማለት ያወግዛሉ በባህሉ መሰረት ዘፈኑ እየተዘፈነ ተጥሶ ወይም ተረግጦ አይከድም፡፡ምህረት ከተደረገለት በኋለ ዘፋኞቹ ጾመኞች እንደመሆናቸው መጠን ስለሚደክሙ ከጸሎትና ምልጃ መልስ ቡና/ቦርዴ እንዲጠጡ በኪሱ ያለውን በመስጠት ተመርቆ ይሄዳል፡፡
ዘፋኞች የያዙትን የምልጃ ቅጠላቅጠልና የለበሱትን ቅርበት ባለው ጅረት/ምንጭ ዉሃ ውስጥ አይጥሉም፡፡ ምክንያቱም የተከሰተው መጥፎ አዲስ ክስተት ከሰፈር እንደይገኝ ተብሎ ስለምታመን ሩቅ ተክዶ ትልቅ ወንዝ ላይ ጥለው እየተንሳፈፈ ሲሄድ እልል..እልል…እልል እያሉ በደስታ እየፈነደቁ ገላቸውን በመታጠብ ከየተኛውም ሀጢአት እንደነጹ በማመን የዘንባባ ዝንጣፊ በመቁረጥ ረጃጅም ብትር መሳይ እንጨት ልጠው በመያዝ የጥዋቱን ሳይሆን አዲስ የምስራች ዘፈን እየዘፈኑና በተሰጣቸው ሳንቲም ቡና/ቦርዴ እየጠጡ በመደሰት ወደዬቤታቸው ይመለሳሉ
ስመለሱም የዘንባባውን ዝንጣፊና የተላጠ ብትር ከሐጢአትና ከመጥፎ ነገር በጸሎትና በምልጃ የነጸና የምስራች ምልክት ነው በማለት እቤት ላሉ ልጆች እንዲሞረኮዙ ያድሏቸዋል፡፡
በዚህም እቤት ልጆችና ሴቶች ቡና በማፍላትና ምሳ በማዘጋጀት አቀባበል ያደርጋሉ፤ ይህ ማለት ሙሉ ነጻነት ለሴቶች በዚህን ወቅት የተኛዉም ተጽኖ ሳይደረግባቸዉ ሙሉ ነጻነት እንዳላቸዉ ያመላክታል።
ይህ ያልተለመደ ክስተት ዘፈን/ዱሞ/ በየሳምንቱ በተከታታይ አራት ዙር ተዘፍኖ የሚጠናቀቅ ሲሆን በዝህም ለዱሞ ዘፈን የእለት ምርጫ ይደረጋል ፣ እነዚህ እለታትም ማክሰኞ፣ ሐሙስ ፣ቅዳሜ እና እሁድ ይሆናል ማለት ነዉ ። ከነዚህ እለታት ዉጭ አይዘፈንም ማለት ነዉ ።
