የሃላላ ኬላ ሎጅ ተደብቆ የነበረውን የቀደምት አባቶች ታሪክ በመግለጥ ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት ፍሰት ከፍተኛ አቅም ፈጥሯል

Spread the love

የሃላላ ኬላ ሎጅ ተደብቆ የነበረውን የቀደምት አባቶች ታሪክ በመግለጥ ለአካባበው ማህበረሰብ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ፍሰት ከፍተኛ አቅም መፍጠሩን የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በገበታ ለሀገር የኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው የሃላላ ኬላ ሎጅ በሚያዚያ 2015 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ይታወሳል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን ግልገል ጊቤ-3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን ተንተርሶ የተገነባው የሃላላ ኬላ ሎጅም በቱሪስት መዳረሻነት የሚያገለግል ድንቅ የመስህብ ስፍራ ሆኗል።

የሃላላ ኬላ ሎጅም ወደ ስፍራው ለሚያቀኑ ቱሪስቶች ታሪክ፣ተፈጥሮና ዘመናዊ የግንባታ ጥበብ ተሰናስለው ውብ ገጽታን በፈጠሩበት አስደናቂ የዓለም አቀፍ የመዳረሻ የተሻለ ጊዜ የሚያሳልፉበትን ዕድል ተፈጥሯል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ÷ ሃላላ ኬላ ቀደምት አባቶች ከ300 ዓመታት በፊት 1 ሺህ 225 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ባለ ሰባት ረድፍ ያለው የድንጋይ ግንብ የገነቡበት ታሪካዊ ስፍራ ነው ብለዋል።

በዚህ መነሻነትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የቀደምት አባቶችን የታሪክ አሻራ በሚገባው ልክ ማስታወስ የሚስያችል የሃላላ ኬላ ሎጅ ኢኮ-ቱሪዝም እንዲገነባ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የሃላላ ኬላ ሎጂም የዳውሮን ህዝብ ታሪክና ልማት በማስተዋወቅ በሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ግንባታ ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

የለውጡ መንግስት ለአካባቢ ማህበረሰብ የፈጠረው የልማት ዕድልም የቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እየተፈጠረ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የሃላላ ኬላ ሎጅ የግልገል ጊቤ-3 የኤልክትሪክ ኃይል ማመንጫን ግድብን ተንተርሶ መገንባቱም ወጣቶች በጀልባ መዝናኛና ሌሎች የስራ ዕድል መስኮች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የሃላላ ኬላ ሎጅ ኢኮ-ቱሪዝም መገንባቱም የዳውሮን ህዝብ ባህላዊ የአመጋገብና የአኗኗር ሥርዓት በማስተዋወቅ በገጽታ ግንባታ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የሎጂው መገንባት ተደብቆ የቆየውን የቀደምት አባቶች የታሪክ አሻራ በመግለጥ በቱሪስት ፍሰት የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።

የዳውሮ ዞን ከሃላላ ኬላ ኢኮ ቱሪዝም በተጨማሪ በዳውሮና ኮንታ ዞኖች መካከል የሚገኘው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ለቱሪዝም ልማት አቅም የሚሆኑ ጸጋዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

በዚህም በዳውሮ ዞን መዋዕለነዋያቸውን ፈሰስ የማድረግ ፍላጎት ያላቸው አልሚ ባለሃብቶች በግብርና፣በሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍ መሰማራት የሚችሉበት ሰፊ ዕድል መኖሩን መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *