




የማህበራዊ ዘርፍ ተቋማት የ2017በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ቀርቦ እየተገመገመ ነው።
በአፈጻጸም ግምገማው የተገኙት የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቤተልሔም ዳንኤል በበጀት ዓመቱ የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠል ውስንነቶችን በመለየት የቀጣይ በጀት ዓመት የዕቅድ አካል አድርጎ መፈጸም ይገባል ብለዋል።
አመራሩ በላቀ አስተሳሰብ በተቋማት የአፈጻጸም ሪፖርት እና ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ለበለጠ ውጤታማነት መምከር ይገባቸዋል ሲሉም ኃላፊዋ ተናግረዋል ።
በማህበራዊ ዘርፍ የትምህርት ፣የሴቶች፣ህጻናት ፣ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣የባህል ስፖርትና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች አፈጻጸምና ጠቋሚ ዕቅድ እያቀረቡ ይገኛል።
የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ደስታ ገነሜ በበጀት ዓመቱ በዕውቀት ፣በክህሎት እና በአመለካከት የተገነባ ብቁና በቂ የሰው ሀይል ለማፍራት ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ በሪፖርታቸው አመላክተዋል ።
በትምህርት ስራዎች የህብረተሰቡን ተሳተፎ በማላቅ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ፣ ከመንግስት ፣ከግለሰቦችና ከትምህርት ቤት የውስጥ ገቢ ከ711.7 ሚሊዮን በላይ ሀብት በገንዘብና በቁሳቁስ ተገኝቶ ስራ ላይ መዋሉን አብራርተዋል ።
የተማሪዎችን የትምህርት ቤት ቆይታ ዘላቂ ለማድረግ በራስ አገዝ የምገባ ፕሮግራም በትምህርት ዘመኑ 44,312 ተማሪዎችን ማሳተፍ መቻሉንም ዶክተር ደስታ ገለጻ አድርገዋል ።
በትምህርት ዘመኑ ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል 746 ሺህ 872 ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን መከታተላቸውን በሪፖርቱ አመላክተዋል ።
በክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል 38,688 ተማሪዎች እንዲሁም 48,072 የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች በዘመኑ ፈተና ላይ መቀመጣቸውንም ገልጸዋል ።
በክልሉ በማህበራዊ ሳይንስና በተፈጥሮ ሳይንስ 19127 ተማሪዎች ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተናን እንዲወስዱ በዩኒቨርስቲዎች መደልደላቸውን ዶክተር ደስታ አብራርተዋል ።
የክልሉ ሴቶች፣ህጻናት ፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ በክልሉ 68325 የሚሆኑ ሴቶች መብትና ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ ትኩረት በመስጠት መሰራቱን ተናግረዋል ።
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ለማሳደግ 93647 ሴቶች የቁጠባ ባህላቸውን አሳድገዋል ብለዋል።
50548 ሴቶች ደግሞ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን በመቅረፍ ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት ተደርጓልም ብለዋል።
የማህበራዊ ዘርፍ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2018 ጠቋሚ ዕቅድ ከየተቋማቱ ቀርቦ ምክክር እየተደረገበት ነው።
በታጠቅ አበበ
