የተሳትፏዊ ግብርናና አየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም ስኬት ተግባራት በቅንጅትና በመናበብ ሊከናወኑ ይገባል-አቶ ማስረሻ በላቸዉ

Spread the love

የክልሉ ግብርና ቢሮ በተሳትፏዊ ግብርናና አየር ንብረት ሽግግግር ፕሮግራም በ2017 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2018 ዓም ዕቅድ ላይ የክልሉ አብይ ኮሚቴ ዉይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸዉ እንደተናገሩት፤የተሳትፏዊ ግብርናና አየር ንብረት ሽግግግር ፕሮግራም እንደየተጠቃሚዉ ፍላጎት እና ስነ-ምህደር ባህሪ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ፍትሃዊና እኩል ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ የግብርና ልማት ሥራዎችን በማካሄድ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዳ በመሆኑ ለፕሮግራሙ ስኬት ተግባራትን በቅንጅትና በመናበብ ማከናወን ይገባል ብለዋል፡፡

ፕሮግራሙ የግብርና ስራዎችን ግብ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በክልሉ የተመረጡ አካባቢዎች የገጠሩን ህብረተሰብ ገቢን በዘላቂነት ማሻሻል፣የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ፣የአየር ንብረት አደጋዎችን የመቋቋም አቅም እንዲገነቡ በማስቻል የክልሉን ምርትና ምርታማነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ፕሮግራሙ የሴቶች፣ወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞችን ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ተሳትፎና ተተቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚበረክት በመሆኑ ፕሮግራሙ ይበልጥ ፍሬያማ ሆኖ ተጨባጭ ውጤት በማምጣት ተጠቃሚዉን ሞዴል ማድረግ እንዲቻል ባለድርሻ አካላት ጠንክረው እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር የተሳትፏዊ አየር ንብረት ሽግግግር ፕሮግራም የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ሰፔሻሊስት በሆኑት አቶ ከፍያለዉ ፀጋ አጠቃላይ የፕሮግራሙ ኣላማና የትግበራ አቅጣጫ ሰነድ አቅርበዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ በተሳትፏዊ ግብርናና አየር ንብረት ሽግግግር ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ታመነ ተስፋዬ በክልሉ ግብርና ቢሮ የተሳትፏዊ ግብርናና የአየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም በ2017 በጀት ኣመት የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርትና የተሳትፏዊ ግብርናና አየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም ቀጣይ ዕቅድ አቅርበው አብራርተዋል።

አቶ ታመነ ተስፋዬ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት እንዳብራሩት፣ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ዉስጥ በመግባት በ2017/18 ምርት ዘመን ለትግበራዉ በተመረጡ አካባቢዎች በፕሮግራሙ የሚከናወኑ ሥራዎችን የማስተዋወቅና የተለያዩ የግብርና ልማት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆታቸዉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በ2018 ዓም የሚተገበረው የተሳትፏዊ ግብርናና የአየር ንብረት ለውጥ ሽግግር ፕሮግራም በሁለት ዞኖች በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች ከ5ሺህ በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አመልክተዋል።

ፕሮግራሙ በልማታዊ ሴፍትኔት የታቀፉ በዳዉሮ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች በልማታዊ ሴፍትኔት ከታቀፉ ስድስት ወረዳዎች ዉስጥ በ3 ወረዳዎች እንደሚተገበር ተናግረዋል፡፡

ለፕሮግራሙ ምርጫ መስፈርቱም ከፍተኛ የመሬት መራቆትና የተፈጥሮ ሀብት መበላሸት፣የህዝብ ብዛት፣የአየር ንብረት ለዉጥ ተጽዕኖዎች፣ከፍተኛ የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ከፕሮጄክቱ ጋር ተያየዥነት ያላቸዉ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎች መኖርን ታሳቢ ያደረገ ነዉ ብለዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት ለማከናወን ከተያዙት ተግባራት መካከል የተለያዩ የስነ-አካላዊ እና የስነ-ህይወታዊ የአፈርና ዉሃ ጥበቃ ልማት ስራ፣የሆርቲካልቸር ችግኝ ጣቢያዎች ግንባታ፤አነስተኛ መስኖ ግንባታ፣የእንሰሳትና ንብ እርባታ፣በዶሮ እርባታ፣በሰብልና በጓሮ አትክልት ልማት ላይ በትኩረት እንደሚሰራም አቶ ታመነ አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ 2017 ዓም ዕቅድ አፈጻጸም ወቀት ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ መፍትኄ ሀሳቦች፣የፕሮግራሙን የቀጣይ 2018 ዕቅድ ለመተግበር የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የሚሳተፉ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር እንዲሁም ትኩረት ሊደረግባቸዉ በሚገባቸዉ ነጥቦች ላይ ዉይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

በካሳሁን አሰፋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *