



በዘንድሮ የመኸር እርሻ 21 ሚሊየን ሄክታር መሬት እንደሚለማ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከኢቲቪ አዲስ ቀን የሀገር ጉዳይ ጋር ቆይታ ያደረጉ ሲሆን ለመኸር እርሻ እየተደረገ ስላለው ዝግጅትም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የመኸር የእርሻ ጊዜ ለኢትዮጵያ ትልቁ የምርት ጊዜ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በአመቱ በአጠቃላይ ከሚመረተው ምርት 70 በመቶ የሚሆነው ከመኸር ውቅት የሚመረት ነው ብለዋል፡፡
በመኸር ወቅት አብዛኛው ግብርና በአነስተኛ ማሳ የሚከናወን ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ 20.3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳ ላይ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
600 ሺህ ሄክታር የሚሆነው ሰፋፊ እርሻና መካከለኛ እርሻ በባለሀብቶች እንደሚለማም ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ 13 ሚሊዮን ሄክታ መሬት በኩታ ገጠም የሚለማ ነው ያሉት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ በአመት ከሚለማው የአነስተኛ ማሳ 20.3 ሚሊየን ሄክተር መሬቱ ከግማሻ በላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም በሚሰራበት ወቅት ምርተማነቱ በ29 በመቶ ጭማሪ እንደሚየሳይ በተለያዩ ጥናቶች መረጋገጡን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
ለመኸር እርሻ በርካታ ዝግጅቶች እንደተደረጉ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ 14 ሚሊየን ሄክተር መሬት የታረሰ ሲሆን በዘር የተሸፈነው 4.3 ሚሊየን ሄክታር መሬት መሆኑን ጠቅሰው ቁጥሩ በየሳምንንቱ እንደሚቀየር ገልፀዋል፡፡
ሁሉም አከባቢዎች ላይ የመኸር ወቅት እኩል አይጀምርም ያሉት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ ግብአት ወደ ክልሎች ሲሰራጭም ይህን ታሳቢ ተደርጎ ነው ብለዋል፡፡
የግብርናውን ሴክተር ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የመጣው ትልቁ ለውጥ የአርሶ አደሮች የቴክኖሎጂን መጠቀም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ አንደሚገኝም ሚኒስትሩ ተናግረዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
