






የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ የወሳኝ ኩነቶች ዘርፍ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሽፋን እና ጥራትን ለማሳደግ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ዉይይት ተካሂዷል፡፡
የዜጎችን መብትና ግዳታ ለማስከበር መሰረታዊ መረጃዎችን ለማደረጃት የሚስችል ተቋም ስለሆነ ለዘርፉ መሳካት በትኩረት እንደሚሰራም ተመልክቷል፡፡
በክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ የጸጥታ ዘርፍ ምክትልና የወሳኝ ኩነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ደነቀ፤የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድ ዝግጅት ባቀረቡበት ወቅት እንዳብራሩት፤በ2017ዓም በ837 ቀበሌያት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሽፋን ለማሳደግ ታቅዶ ሽፋኑን ከዕቅዱ 90 ከመቶ ለመፈጸም መቻሉን ጠቅሰዉ በ2018 በጀት ዓመት በ883 ቀበሌያት የምዝገባ ሽፋኑን ወደ 95 ከመቶ ለማድረስ ዕቅድ መያዙን አስረድተዋል፡፡
የዉይይት መድረኩን የመሩት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ በላይ ተሰማ፤ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዉጤታማነት በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በመስራት የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ ማሳወቅ እንደሚገባ ገልጸዉ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ፤ስራው እንዳሳለጥ ተቋማት የበኩላቸውን አስተዋጾ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡
ቢሮዉ የሚያሰባስባቸዉ መረጃዎች ከክልል አልፎ ለሀገር ትልቅ ጠቀሜታ ያለዉ በመሆኑ የግንዘቤ ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዉ ይህ ሀገራዊ ጉዳይ በመሆኑ ወደ ተግባር ለመቀየር እንዲቻል አስፈላጊዉ ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡
በወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚገኝ ትክክለኛ መረጃ መኖር ለአንድ ሀገር ህዝብ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ መሳካትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው ሁሉም አካል ለዚህ ተግባር ስኬት የየድርሻቸውን ሚና መወጣት እንዳለበትና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የፍ/ቤቶችን ስራ ለማሳለጥ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር፤ከመድረኩ የተገኘዉ የመረጃ ግብዓት የቀጣይ ተግባራትን በተሸለ መልኩ ለመፈጸም እንደሚረዳ ገልጸዉ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቅንጅታዊ አሰራርን የሚጠይቅ ነዉ ብለዋል፡፡
ከሁሉም ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ያለ ቢሆንም ከፍ/ቤቶች እና ከጤና ተቋማት ጋር የተሻለ የስራ ግንኙነት መኖሩን እና በእነዘህ ተቋማት ጋር የበለጠ ትስስር ፈጥረዉ በመስራት ዉጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም አስረድተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የነበሩ ስኬቶችን በማጠናከር እና ክፍተቶችን በመሙላት በተለይም ቅንጅታዊ አሰራሮችን አደራጅቶ ከመምራት አንፃር የሚስተዋሉ ወጣ ገባዎችን ለማስተካከል የሚያስችል መድረክ እንደነበረም ተናግረዋል።
ሁሉም ሴክተር መ/ቤቶች የተቋሙን ዓላማ በሚገባ በመረዳት የማህበረሰቡን መብት ለማስከበርና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅ ጠቁመዉ የተቋሙን ዕቅድ ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር እና በማዘመን የተሻለ ዉጤት ማስመዝገብ እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት ግንባታ በባህሪዉ የሌሎች ተቋማትን ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደመሆኑ መጠን ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን በመለየት በጋራ ለመስራት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ በጋራ ወደ ተግባር በመግባት አፈጻጸሙንም በጋራ እየገመገሙ መምራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በወሳኝ ኩነት የሚመዘገቡ የጋቢቻና ፍቺ ጉዳዮች በፍ/ቤት ለሚወሰኑ የፍቺ ዉሳኔዎች በማህበረሰቡ ዉስጥ የሚፈጠሩ ማህበራዊ ቀዉሶችን ለመቅረፍ የሚያግዝ በመሆኑ ለተግባራዊነቱም በተናበበ መልኩ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተጠቀሷል፡፡
በካሳሁን አሰፋ
