ሪፖርታዥ

Spread the love


የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ ሪፎርም የተቋማትን ዘላቂነት በማጽናት የመንግሥትን የማስፈጸም አቅም የሚያሳድግ ነው፡፡


በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪሲና ሰዉ ሀብት ልማት ቢሮ የተጀመረዉ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ ሪፎርም ተፈጻሚነት ጅምር ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም የሪፎርም መርሀ-ግብር ነድፎ ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ (በየምዕራፉ ከፋፍሎ) እየፈቱ ለመሄድ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም አስፈላጊነት እሙን መሆኑን የክልሉ ተብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ፖሊሲ መነሻዎች ለዘመናት ሲከማቹ የቆዩ እና ስር የሰደዱ የአስተሳሰብ፣ የመዋቅራዊ እና የአፈጻጸም ችግሮች ስርዓቱን አሁን ለተደረሰበት የብቃት ማነስ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት፣የአሰራርና የህግ አለመከበር፣ለሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ሲቪል ሰርቪሱ በድጅታል አሰራር የዘመነ አለመሆኑ፣የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የማዘመን ሥራ፤ በለውጡ ውስጥ የታቀፈውን መሪ ራዕይ ለማሳካት መሆኑን የተናገሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጲያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪሲና ሰዉ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ ናቸዉ፡፡
የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ ከዚህ ቀደም ብሎ እንዳልነበረ እና አሁን የለዉጡ መንግስት ከመጣ ወዲህ የአገልግሎት አሰጣጡን በተሳለጠና በተቀናጀ ሁኔታ ተደራሽ ሆኖ በህዝቡ ዘንድ ያለዉን ምሬት ሊያስቀር በሚያስችል ሁኔታ የተቀረጸ እንደሆነ አቶ ሳምሶን ተናግረዋል፡፡
የሪፎርሙ ዋና ዓላማ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን እንዱሁም ብዝሃነትን እና አካታችነትን ያረጋገጠ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት የሚያቀርብ እና ለክልላዊ የልማት ግቦች ስኬት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ብቁ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት እና የታቀዱ አገራዊ የልማት ግቦችን የሚያሳካና የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጥ ጠንካራ አገረ መንግስት ለመገንባት መሠረት የሚሆን የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር መፍጠር ነዉ ብለዋል አቶ ሳምሶን፡፡
እንደሳቸዉ ገለጻ፤የሪፎርሙ ቁልፍ ጉዳዮች፤የአስተዳደራዊ ሥራዎች ሪፎርም ቀልጣፋና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎት አቅርቦት ሥርዓትን መዘርጋት፤የመንግሥት ሠራተኞች የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ሥርዓት መገንባትና የማስፈጸም አቅምን ማሳደግ፤ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት ቅቡልነት ያላቸው አገልግሎቶችንና ውሳኔዎችን ማቀላጠፍ፤ ነፃና ገለልተኛ የሲቪል ሰርቪስ ግንባታን ማሳለጥ፤ የሲቪል ሰርቪስ ገቢር ነበብ አመራር እና ተቋም ግንባታን ማፋጠን እንዲሁም ብዝኃነትንና አካታችነትን ያረጋገጠ ሲቪል ሰርቪስ ግንባታን ማፋጠን ናቸዉ፡፡
ይህም በሶስት ምዕራፎች ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በመጀመሪያዉ ምዕራፍ ስምንት ተቋማት፤ በሁለተኛዉ ምዕራፍ ዘጠኝ እንዲሁም በሶስተኛዉ ምዕራፍ ሰባት ተቋማት ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ያሉት ኃላፊው በምዕራፍ አንድ የዝግጅት ጊዜ ለአንድ ዓመት፤ በምዕራፍ ሁለት አንድ ዓመት ከ6ወር የትግበራ ጊዜ፤ በምዕራፍ ሶስት ለ6 ወራት የማጽናትና ማዝለቅ ሥራ የሚከናወን ይሆናል ብለዋል፡፡
በዝግጅት ምዕራፍ የሚተገበሩ ስራዎች ደግሞ የሪፎርሙ መሠረታዊ ተግባራት የሆኑት ተቋሙ ወይም ዘርፉ የሚመራበትን ፖሊሲ መፈተሽ፤ የዘርፉን ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች፣ ስታንዳርዶች፣ ማኑዋሎች እና የሕግ ማዕቀፎችን መፈተሽ፣ ከአገራዊ ሁኔታ በመነሳት ጥንካሬዎችን፣ ድክመቶችን፣ እድሎችን እና ስጋቶችን በመለየት ስለ ዘርፉ አሁናዊ ሁኔታ ጥልቅ ትንተና በማካሄድ የዘርፉን የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ማዘጋጀት፣፤ሰራተኞችን ስለ ሪፎርሙ ዓላማ ለማስተዋወቅ ተገቢውን ግንዛቤ በመያዝ እንዲነሳሱ በዕምነትና በንቃት እንዲደግፉና እንዲሳተፉ ለማድረግ እና በተቋሙ የለውጥ ድባብ ለመፍጠር እንዲቻል አስፈላጊ ስልጠናዎችን ማካሄድ እንዲሁም የሪፎርሙን ዓላማዎች እና ግቦችን በውል እንዲረዱ ማድረግ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ሪፎርሙ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ እና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ይህም በሙያ ምደባ፣ በሥራ ምዝና፣ በክፍያ ሥርዓት እና በመረጃ ሥርዓት ይታይ የነበረውን ችግር በመፍታት የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት የሚያረካ፣ የመንግሥትን አገልግሎት እና አሥተዳደር ሥርዓት የሚፈጥር መኾኑን የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪሲና ሰዉ ሀብት ልማት ም/ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ ጠቅሰዋል፡፡
ከለውጥ መንግስት በኋላ የተቋማት ሪፎርም ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ወቅታዊ ሀኔታዎችን ያገናዘበ ለዉጥ መጀመሩ መልካም ነው ያሉት አቶ ሳምሶን በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥና የብልሹ አሰራር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል በመሆኑ ተግባራዊ ማድረግ ከሁሉም የስራ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች ይጠበቃል ብለዋል።
የሪፎርም ሥራዎችን ተቋማዊ መሰረት ለማስያዝና ውጤታማ ለማድረግ፣መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንዲሁም ለውጡን በሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ፣የሰው ሀይል ልማትና ስምሪት ፍትሀዊነትና ውጤታማነት ለማረጋገጥ፤ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ለማምከን ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አዉስተዉ ሪፎርሙ ሀገራችን በአጭር፣በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለማከናወን ያስቀመጠቻቸውን ግቦችን ለማሳካት እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡
ለሲቪል ሰርቪሱ ሪፎርም ትግበራ የተዘጋጀ ጥቅል ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሰነድ ላይ በሪፎርሙ የሚካተቱ የክልል ቢሮዎች፣ለዞን መምሪያ ኃላፊዎች እና ሙያተኞ በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲና በክልሉ ፍኖተ ካርታ ላይ በቦንጋ ከተማ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡
በካሳሁን አሰፋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *