ሪፖርታዥ

Spread the love

በክልሉ የህዝብ ቁጥር ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው፦ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ

በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣው የህዝብ ቁጥር ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማስቻል መንግስት በሥነ-ሕዝብ ጉዳዮች ላይ የመስራትን አስፈላጊነት በመረዳት በ1985 ዓ.ም ብሔራዊ የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ እንዲቀረፅ በማድረግ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ፖሊሲው ተግባራዊ በተደረገባቸው ባለፉት 32 ዓመታት ከሁለንተናዊ ዕድገት አኳያ በርካታ ለዉጦች መጥተዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ም/ የቢሮ ኃላፊ እና የመረጃ እና ስነ ህዝብ ልማት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታምራት መኩሪያ፤ በክልሉ እየታየ ያለው ፈጣን የሕዝብ ቁጥር በሚካሄዱ ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊና አሉታዊ ጫና እያሳደረ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህንን ጫና ለመቅረፍ ያስችል ዘንድ በክልሉ የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲዎችን ከልማት እንቅስቃሴ ጎን ለጎን የህዝብ ቁጥር ዕድገቱን መመጠን የሚያስችል ተግባር እየተተገበረ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ ይፋ ሆኖ ተግባራዊ እንዲሆን ካደረጓቸው ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ፤ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት መኖርና በሌላ በኩል ደግሞ ዝቅተኛ ምርትና ምርታማነት በግብርናው፣በኢንዱስትሪውና በአገልግሎት ዘርፍ መኖር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱም ሆነ በክልላችን እየታየ ያለውን ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ከልማት ዕድገትና ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን በማድረግ ድህነትን ደረጃ በደረጃ በመቀነስ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑንም አቶ ታምራት አብራርተዋል፡፡

የሥነ ህዝብና ልማት ትስስር ውጤታማ ለማድረግ በክልሉ የሚገኙትን ሁሉንም የልማት አቅሞች ማለትም፡-የሰው ጉልበት፣ እዉቀት፣ መሬትና እና የተፈጥሮ ሀብት በማቀናጀት የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚሰራ መሆኑን ነው የገለጹት ፡፡

በገቢው መጠን የተሟላና ደስተኛ ኑሮን መኖር የሚችል ህብረተሰብ ለመገንባት የህዝብ ቁጥር እድገት ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር መጣጣም ያለበት ከመሆኑ አኳያ ስነ ህዝብና ልማት የተሳሰሩ ጉዳዮች መሆናቸውን መረዳት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል ፡፡

የክልሉ ፈጣን ህዝብ ቁጥር እድገት በኢኮኖሚ፣በማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት አንጻር ያለዉን አሉታዊ ተጽእኖ ስንመለከት ተቋማት በበቂና በጥራት ለማህበረሰቡ ተገቢዉን አገልግሎት እንዳይሰጡ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል ነው ያሉት አቶ ታምራት መኩሪያ ፡፡

በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣው የሕዝብ ቁጥር የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ህብረተሰቡ ጥራት ያለው ህክምና እንዳያገኝና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ በማዳረስ ጤናማና ብቁ ዜጋን ከማፍራት አንፃር እንቅፋት የሚሆን መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የክልላችንን ነባራዊ ሁኔታ ከጤና ተቋማት አንፃር በክልሉ ለ3,837,201 ህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ሪፈራል ሆስፒታል የሌለ መሆኑን ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አቶ ታምራት ገልፀዋል፡፡

ከትምህርት አኳያ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት አብዛኛው ትምህርት ቤቶች ስታንዳርዱን የጠበቀ የቤተ ሙከራ፤የቤተ መጽሐፍት፤የአይ ሲቲ ማእከልና ሌሎች መመሪያና ማጣቀሻ መጽሐፍት ያለመኖር በተማሪ ውጤት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ በቀጣይ በሰፊው መስራት የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣ የሕዝብ ቁጥር ንጹህ መጠጥ ዉሃ ተደራሽነትና ጥራት ላይ ተቋማት በስታንዳርዱ መሰረት አገልግሎት እንዳይሰጡ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ህብረተሰቡ ንጹህ የመጠጥ ዉሃ እንዳያገኝ እንቅፋት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ንጹህ የመጠጥ ዉሃን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የገጠርና ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሽፋን በአማካይ ወደ 42.8 ማድረስ የተቻለ ቢሆንም በከተማም ሆነ በገጠር የንጹህ መጠጥ ዉሃን ለሁሉም የክልሉ ማህበረሰብ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ብዙ የሚቀረንና ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን አቶ ታምራት አመላክተዋል፡፡

በክልላችን ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ ከጊዜ ወደ ጊዜ በቤተሰብ ደረጃ ያለው ለእርሻ የሚሆን የመሬት ይዞታ እያነሰ መሄድ ፣ የሕዝብ ጥግግቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መምጣት፣ የመሬት ለምነት መቀነስ ችግር እያስከተለ ይገኛል ብለዋል፡፡

የሥነ-ሕዝብ ልማት ፖሊስ ማሻሻያ ያለመደረጉ፣ ሕዝቡን ማዕከልና ባለቤት ያለማድረግ፣ የተቀናጀ አሠራር ያለመኖር፣ ቁርጠኝነት ማነስ ችግር፣የተጠናከረ የትብብር መንፈስ ያለመኖር፣ በተጠያቂነትና ኃላፊነት ተግባራትን ያለመምራት ችግሮች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ታምራት፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በየደረጃዉ የስነ-ህዝብ ም/ቤት በማቋቋም በተቀናጀ መንገድ እየተመራ ነው ያሉት፡፡

የስነ ህዝብ ጉዳይ ሁሉን አቀፍ ተግባር በመሆኑ ደንብ ወጥቶለት በደንቡ መሰረት ም/ቤት በማቋቋም በክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር እንዲመራና በተዋረድ ያሉ ም/ቤቶች በዋና አስተዳዳሪዎች እንዲመሩ በማድረግ በሁሉም የአስተዳደር እርከን የሥነ ህዝብ ጉዳይ ተግባራት ትኩረት እንዲያገኙ መደረጉንም አቶ ታምራት ጠቁመዋል ፡፡

የሥነ ህዝብ ጉዳይ ሥራዎች በልማት ዕቅድ ዉስጥ አካትቶ ማከናወን ላይ ያሉ መሰረታዊ ችግሮች በም/ቤቱ እየተገመገመ የሚፈቱበት አግባብ እንዲፈጠር በባለድርሻ ተቋማት የዕቅድ አካታችነት እንዲረጋገጥ ማድረግ ይኖራልም ብለዋል፡፡

በክልላችን ደረጃም ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ያልተመጣጠነ የህዝብ ቁጥር እድገት በሚካሄዱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ የራሱን ጫና እያሳደረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የሥነ-ሕዝብ ጉዳይ በአንድ መሥሪያ ቤት ብቻ ተሠርቶ የሚጠናቀቅ ተግባር ያለመሆኑ ን ያነሱት አቶ ታምራት ተቋማት የልማት እቅድ ውስጥ የሥነ-ሕዝብ ጉዳይን መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በየደረጃዉ ያለዉ የሥነ ህዝብ ምክር ቤት አባላት በሥነ-ሕዝብና ዘላቂ ልማት መካከል ያለውን ጥልቅ መስተጋብር በመረዳት ሁሉም በቅንጅት በመሥራት እና የክልሉ ህዝብ ቁጥር ዕድገት ከኢኮኖሚዉ ዕድገት ጋር እንዲጣጣም እያንዳንዱ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *