




ረቂቅ የበጀት አዋጁን የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ የኋላሸት በላይነህ ለምክርቤቱ አቅርበዋል።
የቀረበው በጀት ከክልል ገቢ የሚሰበሰብ፣ከፌዴራል መንግስት ድጎማና ከሌሎች የገቢ ምንጮች የሚገኝ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አብራርተዋል ።
በዚህም መሠረት ለክልል ማዕከል መ/ቤቶች መደበኛና የካፒታል ወጪ 2.2 ቢሊዮን ፣
ለዞኖች ጥቅል በጀት 23.5 ቢሊዮን ፣
ለክልላዊ ፕሮግራሞች 2.2 ቢሊዮን ፣
ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ 436.8 ሚሊዮን
ለክልሉ መጠባበቂያ በጀት 2 መቶ ሚሊዮን በአጠቃላይ የ2018 በጀት ዓመት 28 ቢሊዮን 677 ሚሊዮን 427 ሺህ 686 ብር ከ70 ሳንቲም ሆኖ እንዲጸድቅ ክብርት ወ/ሮ የኋላሸት በላይነህ ለምክርቤቱ አቅርበዋል ።
የበጀት ምንጩ ከፌዴራል መንግስት ግምጃቤት ፣ከውጭ እርዳታ ፣ከዘላቂ ልማት ግቦች ፣ ከመደበኛ ገቢ፣ከጤና ተቋማት፣ከማዘጋጃ ቤት ገቢ፣ከትምህርት ቤቶች ገቢ እንደሚሰበሰብም አብራርተዋል።
በቀረበው ዝርዝር የበጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ በምክር ቤቱ አባላት አስተያየቶች ተነስተዋል ።
የምክርቤት አባላት የቀረበው የበጀት ዕቅድና ወጪ ከአምናው በጀት ዓመት መሻሻሎች የተያበት በመሆኑ ከማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት የሚሰበሰበውን በጀት የገቢ አማራጮችን በማስፋት ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰበሰብም ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግስት ፋይናንስ ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ በሰጡት ማብራሪያ የክልሉን ገቢ ለመሰብሰብ ያሉንን የገቢ አማራጮች በመጠቀም ግቡን ማሳካት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የበጀት ምንጩ 18.4 ቢሊየን ከክልላዊ ገቢና 10.2 ቢሊየን ከፌዴራል መንግስት ግምጃቤት ፣ከውጭ እርዳታ ፣ከዘላቂ ልማት ግቦች እንደሆነም ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ አብራርተዋል ፡፡
የበጀት ገቢ ዕቅድን ውጤታማ ለማድረግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ከበጀቱ 65 በመቶ የሚሆነው ለካፒታል ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ላይ ትኩረት እንደሚደረግበትም አብራርተዋል ፡፡
በረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳው ሀሳብ እና አስተያየት ምላሽ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የቀረበው የ2018 በጀት ዓመት የበጀት ዕቅድ በ11 ቢሊየን ብልጫ ከፍ ብሎ መታቀዱን ተናግረዋል ፡፡
የገቢ አሰባሰቡ ውጤታማ እንዲሆን ክልላዊ የገቢ አማራጮችን በመጠቀም መሰብሰብ ይገባል ብለዋል።
ከተያዘው የ2018 በጀት ዓመት 82 ከመቶ የሚሆነው ለታችኛው መዋቅር እንዲሁም 18 ከመቶ የሚሆነው ለክልል ድርሻ መያዙንም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል ፡፡
ለክልል ድርሻ ከተያዘውም 57 ከመቶ የሚሆነው ለዋና ዋና መሰረታዊ ካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚ እንደሚውልም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ፡፡
በጀቱንም ለሰብዓዊ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት እንዲሁም ከሌብነት፣ከብክነትና ከብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ የፋይናንስ መመሪያና ደንብን ተከትሎ ስራ ላይ ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በ6ኛ ዙር 4ኛ የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ የቀረበው የ2018 በጀት ዓመት 28.6 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የቀረበውን ረቂቅ በጀት አዋጅ የምክርቤት አባላት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
በታጠቅ አበበ
