




የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2018 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በአቶ ቆጭቶ ገብረማርያም ቀርቧል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማሪያም ለምክርቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ፍርድ ቤቶች ነጻና ገለልተኛ ሆነዉ የዳኝነት አገልግሎት መስጠታቸው ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ ፍርድቤቶች የተሰጣቸውን ህግ የመተርጎም ስልጣንን መሰረት በማድረግ የዜጎች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ፣የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና እንዲከበር የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉም ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ካለፈው በጀት ዓመት የተሻገሩና በ2017 በጀት ዓመት የቀረቡ አዳዲስ የወንጀልና የፍትሐብሔር መዝገቦችን ጨምሮ 61ሺህ 932 መዝገቦች ቀርበው 60ሺህ 441መዝገቦች ላይ ውሳኔ መስጠት መቻሉን የጠቅላይ ፍርድቤቱ ፕሬዝደንቱ አቶ ቆጭቶ ገ/ማሪያም አብራርተዋል ።
በበጀት ዓመቱ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናንና ዉጤታማነትን ማሳደግ፣ የዳኝነት ነፃነት እና ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት፣የባህላዊ ዳኝነትን በማጠናከር በየደረጃዉ ባሉ ፍርድ ቤቶች የተሻለ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቶች ነጻና ገለልተኛ ሆነዉ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት የመንግሥት የተፋጠነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት፣የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ዕቅዶች እንዲሳኩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንም አብራርተዋል።
የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናንና ዉጤታማነትን በማሳደግ፣ የዳኝነት ነፃነት እና ተጠያቂነት በማረጋገጥ ፣ የአገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ተቋማዊ መፈጸምና ማስፈጸም አቅም ማሳደግ መቻሉንም ገልጸዋል።
በቀረበው የጠቅላይ ፍርድቤት የአፈጻጸም ሪፖርት የምክርቤት አባላት አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማ እንዲሆንም ተጠናክሮ ሊሰራበት እንደሚገባ የምክርቤት አባላት ጠይቀዋል።
የጠቅላይ ፍርድቤቱ የስራ አፈጻጸም የተሻለ መሆኑንና የዳኝነት አገልግሎቱ ቀልጣፋና ተደራሽ መደረጉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ከምክርቤቱ አባላት ለቀረቡ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማሪያም ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የቀረበውን የጠቅላይ ፍርድቤት ሪፖርትና ጠቋሚ ዕቅድ የምክርቤት አባላት በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል።
በታጠቅ አበበና በካሳሁን አሰፋ
