



ምክርቤቱ የክልሉ ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2018 ዓ/ም ጠቋሚ ዕቅድ ላይ መክሯል።
የክልሉ ዋናው ኦዲትመስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ አስራት አበበ በ2017 ዓ/ም በተመረጡ የመንግስት መ/ቤቶችና ድርጅቶች ላይ የተከናወኑ የኦዲት ስራዎችን ሪፖርት ለምክርቤቱ አቅርበዋል።
በቀረበው የኦዲት ሪፖርት በበጀት ዓመቱ በ35 ተቋማት የፋይናንሻልና ህጋዊነት ኦዲት እንዲሁም የ2016 ዓ/ም የክልሉ መንግስት የተጠቃለለ ገቢና ወጪ ሂሳብ ኦዲት መደረጉን በሪፖርቱ ጠቅሰዋል ።
የኦዲት ውጤት ተፈጻሚነት አንጻር በ41 መ/ቤቶች በኦዲት አስተያየት መሠረት በወቅቱ ምላሽ መሰጠቱንና ተገቢው እርምት ስለመወሰዱ ክትትል መደረጉን አቶ አስራት አብራርተዋል ።
የክዋኔ ኦድት አፈጻጸምን በሚመለከት በዞን ምክር ቤቶች ጉባኤ በተደጋጋሚ ጥያቄ በሚነሱባቸው በተለዩ 6 በሂደት ላይ ባሉ ፕሮጀክቶች የክዋኔ ኦዲት መደረጉንም አቶ አስራት ገልጸዋል ።
የፉይናንሻልና ህጋዊ ኦዲት አንጻር በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የጥሬ ገንዘብ ቆጠራ ሚዛንና በሪፖርት የተላለፈ የጥሬ ገንዘብ ሚዛን እኩል ስለመሆኑ ለማረጋገጥ በ35 መ/ቤቶች በተደረገው ኦዲት በ11 ተቋማት በሳጥን ቆጠራና በተላለፈው ሪፖርት የጥሬ ገንዘብ ሚዛን ልዩነት መታየቱን በሪፖርቱ አብራርተዋል ።
መመሪያን ተከትሎ ክፍያዎችን ከመፈጸም አኳያ በአንዳንድ መስሪያቤቶች ክፍተቶች መኖራቸውን ያመላከቱት አቶ አስራት የተለያዩ ክፍያዎች ሲፈጸሙ የፋይናንስ መመሪያን በመከተል ሊሆን እንደሚገባ በሪፖርቱ አመላክተዋል።
በኦዲት ማሻሻያ ሀሳቦች ላይ ማስተካከያዎችን ከመውሰድ አኳያ ከ2014 እስከ 2016 ዓ/ም ኦዲት ተደርገው ከተሰጡ አስተያየቶች በጥሬ ገንዘብ ወደ መንግስት ካዘና 19,830,210.47 ብር ተመላሽ ተደርጓል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በተደረገው የኦዲት አገልግሎት የግዢ፣ የንብረት ገቢና ወጪ፣ የድጎማና ድጋፍ አሰጣጥ ሂሳቦች መሻሻል ያሳዩ መሆናቸውንና የሂሳብ ምዝገባና ሪፖርት ስርዓት አሁንም ችግሮች እንዳሉበት አቶ አስራት አስታውቀዋል።
በቀረበው የክልሉ ዋናው ኦዲተር መስሪያቤት የ2017 ዓ/ም አፈጻጸም ላይ የምክርቤት አባላት አስተያየት እና ጥያቄዎችን አንስተዋል ።
የምክርቤት አባላት ባነሱት አስተያየት የክልሉ ዋናው ኦዲት መስሪያ ቤት የጀመራቸው ስራዎች በርካታ ሀብትን ከብክነት መታደግ የተቻለበት በመሆኑ አሰራሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል ።
በተነሱ አስተያየቶች ላይ የክልሉ ዋናው ኦዲተር መስሪያቤት ዋና ኦዲት አቶ አስራት አበበ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የምክርቤት አባላትም በቀረበው የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2018 ዓ/ም ጠቋሚ ዕቅድን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
በጌታሁን ግርማና በታጠቅ አበበ
