




የተቋሙን ሪፖርት ዋና ስራአስኪያጅ አቶ መንግስቱ መኩሪያ ለምክርቤቱ አቅርበዋል።
ባቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት ሚዲያ ኔትወርኩ በማህበራዊ የሚዲያ አማራጮች መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ተቋሙ የክልሉን ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በተዘረጉ የማሰራጫ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል ።
ሚዲያው በተሟላ አቅሙ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ተቋሙን በሰው ኃይልና በቁሳቁስ ለማሟላት ጥረቶች መደረጋቸውን አቶ መንግስቱ ገልጸዋል።
ሚዲያ ኔትወርኩ ባለፉት ስድስት ወራት በመረጃ የበለጸገ ህብረተሰብን ከመፍጠርና በህዝብና መንግስት መካከል ድልድይ ሆኖ ለማገልገል ዘርፌ ብዙ ተግባራትን ሲያከናወን መቆየቱን አቶ መንግስቱ ገልጸዋል።
በቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት የምክርቤት አባላት ባነሱት አስተያየት የክልሉን እምቅ ጸጋዎችንና ሀብቶች ገልጦ ለዓለም ከማሳወቅ አንጻር ተግቶ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
ሚዲያው የክልሉ ትሩፋት መሆኑን ያነሱት የምክርቤት አባላት ይበልጥ ተደማጭና ተደራሽ ለመሆን በፍጥነት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ሚዲያው ከሌሎች የሚዲያ ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት በሚዲያ ቴክኖሎጂ ራሱን ማብቃት ይኖርበታል ብለዋል።
በቀረበው የምክርቤት አባላት አስተያየት ላይ የተቋሙ አፈጻጸም ላይ በተነሱ አስተያየቶች ተቋሙ የበለጠ ተስፈንጥሮ ወደፊት ለመውጣት የሚያግዝ ገንቢ አስተያየት መሆኑን አቶ መንግስቱ ተናግረዋል ።
ተቋሙን በሚዲያ ቴክኖሎጂ ለማደራጀት ትልቅ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ ህብረተሰቡ እና የመንግስትን ድጋፍ ይሻል ብለዋል።
የተለያዩ ለተቋሙ የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማሟላት ከተለያዩ የክልልና ፌደራል ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን በመግለፅ ተቋሙ በሙሉ አቅሙ ስራውን እንዲያከናውን የም/ቤቱ አባላት ድጋፍ እንደሚሻ ጠይቀዋል ።
በቀጣይም ሚዲያው በሬዲዮና በቴሌቪዥን ስርጭት ለህዝብ ተደራሽ ለመሆን ዕቅድ መያዙንም አቶ መንግስቱ መኩሪያ ለምክርቤቱ አቅርበዋል።
የክልሉ ምክርቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ ሚዲያው ውጤታማ እንዲሆን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ያስፈልገዋል ብለዋል።
በቀረበው የሚዲያ ኔትወርክ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትና የ2018 ዓ/ም ጠቋሚ ዕቅድ ቀርቦ በምክርቤት አባላት በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።
በታጠቅ አበበ
