




በውይይቱ ከምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችና በግብዓትነት የሚወሰዱ ሀሳቦች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት የቀረቡ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች አስተማሪና በዝርዝር ዕቅድ በማካተት በቀጣይ የሚከናወኑ መሆናቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ያባለፈው ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀና እስካሁን ያልተፈቱ የህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችንና የመልማት ፍላጎትን ለመፍታት ትኩረት በመስጠት የታቀደ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
ዕቅዱ የክልሉ የመልማት አቅምና ዕምቅ ሀብቶችን ታሳቢ ያደረገና ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራተዋል።
በግብርናው የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥም በላይ በቡና እና ቅመማ ቅመም፣ ሻይ፣ በቅባት እህሎችና ሌሎች ገበያ ተኮር ክልሉን ማስተዋወቅ በሚችሉ ምርቶች ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ተናግርዋል።
በአርሶ አደር ዘንድ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ዓይነተኛ ሚና ያላቸው እንደ እንሰት እና አሲዳማነትን መቋቋም በሚችሉ እንደ ካሳባና ሌሎች የስራስር ምርቶች ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በክልሉ የአደጋ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በዕቅድ እንዲሚሰራም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በክልሉ የሚሰሩ የመንገድ መሠረተ ልማትን ውጤታማ ለማድረግ
ክፍተቶችን በማረም አስፈላጊ የሰው ኃይልና ማሽኖችን አቅም በፈቀደው መጠን በማሟላት በትኩረት እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራተዋል።
በፌደራል ፕሮጀክት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ላይ ክትትልና ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማንሳት በየደረጃው ያሉ መዋቅሮችና ህዝቡ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በጤና ዘርፍ የወባ ወረርሽኝን በመከላከል የተጀመሩ ስራዎችና ሌሎች የህብረተሰቡን ጤና ሊያስጠብቁ የሚችሉ የጤና ተግባራት ተጠናክረው በቅንጅት እንደሚሰሩ ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።
የትምህርት ዘርፉን ስብራት በመጠገን ጥራቱን ለማሻሻል በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄና በህብረተሰብ ተሳትፎ እንዲሁም በመንግስት የተጀመሩ ስራዎች ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላሉ ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ ።
ሞደል የህብረት ስራ ማህበራትን በመፍጠርና በማጠናከር ቁጠባን ባህል በማድረግ እንዲሁም ብድርን በተገቢው በማሰራጨትና የገበያ ትስስርን የማጠናከር ሥራ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በመጨረሻም የ2018 ዓ/ም የአስፈጻሚ ተቋማት ዕቅድ በምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
በጌታሁን ግርማ
