


በ2017 በጀት ዓመት አስፈጻሚ አካላት በምክር ቤቱ የተነሱ ጉዳዮችን በተገቢው ማከናወን የቻሉበት እንደሆነም የምክርቤቱ አባላት ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክርቤት 6ኛ ዙር 4ኛ የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ማምሻውን ተጠናቋል።
በጉባኤው የተሳተፉ የምክርቤት አባል የተከበሩ ወ/ሮ ገነት መንገሻ በግብርና እና በፕሮጀክቶች የተሻለ አፈጻጸም መኖሩንም ገልጸዋል።
በተከናወነው የበጀት ዓመት በትምህርት፣በጤናና በገቢ አሰባሰብ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑንም ወ/ሮ ገነት ተናግረዋል ።
በቀጣይ በጀትም በግብርናው፣በመንገድ፣በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣በጤናና በትምህርት ዘርፎች አሁንም ልዩ ትኩረት በመስጠት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም የታየበት ነው ሲሉ የተከበሩ አቶ ጨነቁ ኮንታር ተናግረዋል ።በተለይም በግብርናው በጤና በትምህርት ስራዎች ለውጦች የተገኙበት መሆኑንም አቶ ጨነቁ ተናግረዋል ።
ከጤና አኳያ በተለይም የወባ ወረርሽኝን ለመከለካል በክልሉ የተደረገው ሁሉአቀፍ ርብርብ የተሻለ መሆኑን በመግለጽ አሁንም ያለውን ስጋት ለመቀነስ የሌሎች አካላትን ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል።
የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የተሄደበት ርቀት የሚደነቅ ነው ያሉት አቶ ጨነቁ በሂደት ላይ ያሉ እንዲጠናቀቁ የህብረተሰቡም ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
ሌላይኛው አስተያየት የሰጡት የተከበሩ አቶ ተክሌ ተሰማ በበጀት ዓመቱ በክልሉ የተያዙ ዕቅዶች ጥሩ አፈጻጸም የታየባቸው መሆኑን ገልጸዋል ።
የተገኙት ስኬቶች የአመራሩን ቁርጠኝነት በተሞላው ተግባራትን የመምራት ብቃት እየጨመረ መምጣቱን ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
አስተያየት የሰጡት የምክርቤት አባላት በቀጣይ በጀት ዓመት መንግስት ላቀዳቸው የልማት ዕቅዶች ውጤታማ እንዲሆኑ ከህብረተሰቡ ድጋፍን ይሻል ብለዋል።
በታጠቅ አበበ
