የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?

Spread the love


ባለፉት ተከታታይ ወራት ‘’የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?’’ በሚል አምድ ሥር አጠቃላይ የክልላችንን ገጽታ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ የካፋ፣ የዳዉሮ፣ የቤንች ሸኮ እና የሸካ ዞኖችን አጠቃላይ ገጽታን የሚያሳዩ፤ የካፋ ባህላዊ ዱሞ ስርዓት፣ የዳውሮ ዱቡሻ ስርዓትንና የኮንታ ህንግጫ በዓልን የቃኙ ጽሁፎችን እንደየቅደምተከተላቸው ለውድ አንባቢያን አጋርተናል፡፡ አሁን ደግሞ የሸካቾ ብሔረሰብ ባህላዊ የለቅሶ ስርዓትን እንቃኛለን፡፡ መልካም ንባብ!”
የሸካቾ ብሔረሰብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ስር ከሚገኙ ከ13 ነባር ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ብሔረሰብ ከሌሎቹ የሚጋራቸው የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች እንዳሉት ሁሉ፣ የብሔሩ መገለጫ የሆኑ ልዩ ልዩ ባህላዊ እሴቶችም አሉት፤ ከሚለዩት ባህላዊ መገለጫዎች መካከል የለቅሶ ስርዓት አንዱ ነው፡፡
የለቅሶ ስርዓት በሸካቾ ብሔረሰብ እንደአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የለቅሶ ስርዓት ሁሉ እድሜን፣ ፆታን፣ ማህበራዊ ደረጃን እና ኢኮኖሚያዊ አቅምን መሰረት አድርጎ በአንዳንድ የአከዋወን ስርዓቶቹ ላይ የሚለያዩ ነጥቦች ይስተዋሉበታል፡፡ ይሁን እንጂ የሸካቾ ብሔረሰብ ሰፋ ያለ ባህላዊ የለቅሶ ስርዓት የሚያከናውነው አንድ አይነት ባህላዊ የስልጣን ባለቤት ለሆኑት እና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ከፍ ላለ የህብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በብሔረሰቡ ባህል መሰረት ጥርስ ያላበቀለ ህፃን ልጅ ሲሞት የሚኖረውም ስርዓትም የተለየ ነው፡፡
የሸካቾ ብሔረሰብ ባህላዊ የለቅሶ ስርዓት ክዋኔን (በሸክኛ “ሸኪ ኤፎ” ይባላል) ማህበረሰቡ ከሚያስቀምጣቸው የልዩነት ነጥቦች አንፃር ከሌሎቹ የብሔረሰቡ አባላት የተለየ የሚባለው የለቅሶ ስርዓት የሚፈፀመው ጥርስ ሳያበቅሉ በሞት ለሚነጠቁ ህፃናት የሚደረገው የለቅሶ ስርዓት ነው፡፡
ከዚህ ውጭ ለንጉስ፣ ለጎሳ መሪዎች እና ለቃልቻዎች የሚደረገው የለቅሶ ስርዓት አንድ ባለፀጋ ሲሞት በሚደረገው የለቅሶ ስርዓት ላይ የተወሰነ የሚጨምረው ነገር ቢኖረውም አብዛኛው ገፅታው ተመሳሳይ ነው፡፡ እንዲሁም ከፆታ አንፃር ለሴቶቹም ሆነ ለወንዶች የሚደረገው የለቅሶ ስርዓት አብዛኛው ገፅታው ተመሳሳይ ሆኖ በተወሰኑ ክዋኔዎች ላይ ግን ልዩነት ይስተዋልበታል፡፡
ለእያንዳንዱ አካላት የሚደረገው ለቅሶ እንዲደምቅ አሊያም እንዲደበዝዝ ዋነኛውን ሚና የሚጫወተው ሟች ወይም የሟች ቤተሰቦች ያላቸው ኢኮኖሚያዊ አቅም መሆኑንና በመሆኑም የብሔረሰቡን ባህላዊ የለቅሶ ስርዓት የአከዋወን ሂደት “ለህፃናት የሚደረግ የለቅሶ ስርዓት” እና “ለአዋቂዎች የሚደረግ የለቅሶ ስርዓት” በሚል ሁለት አበይት ጎራ የሚከፈል ነው፡፡


ለህፃናት የሚደረግ የለቅሶ ስርዓት፦
በሸካቾ ብሔረሰብ ልጅ የሞተው ጥርስ ሳያበቅል ከሆነ ነፍሱ ባለፈችበት ቅፅበት ቤተሰብ እና ጎረቤት ብቻ እርምን ለማውጣት ያህል ብዙም ከፍ ባላለ ድምፅ አልቅሰው ሟችን ይሰናበታሉ፡፡ የቀብር ስርዓቱም በሌላው የዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ የህብረተሰቡ ክፍሎች ፈፅሞ ይለያል፡፡ ጥርስ ሳያበቅሉ ለሞቱት ህፃናት ከቀብር በፊት፣ በቀብር ጊዜ እና ከቀብር በኋላ የሚከወኑ ስርዓቶችን ይኖሩታል፡፡ አንድ ህፃን የእናቱን ጡት እየጠባ፣ ከእናቱ እቅፍ ሳይወርድ በተለያዩ ምክንያቶች ቢሞት በሸካቾ ብሔረሰብ ባህል መሰረት ቀብሩ የሚፈፀመው መሬት ውስጥ ሳይሆን ዛፍ ተቦርቡሮ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን የተፈለገበትን ምክንያት እንደ ብሔረሰቡ እምነት ጥርስ ሳያበቅል የሞተው ህፃን ልጅ መሬት ውስጥ ከተቀበረ እናትየው ዳግም አትወልድም ተብሎ የሚታመን በመሆኑ ነው፡፡ ህፃን ልጃቸውን በሞት የተነጠቁት ሴት ቤተሰቦች እና ጎረቤቶች በጋራ በመሆን በለሆሳስ አጠር ያለ ለቅሶ በማልቀስ እርማቸውን ያወጣሉ፡፡ ከዚህን በኋላ ከቤተሰቡ ወይም ከጎረቤቱ መካከል በዕድሜ ጠና ያሉ አዛውንቶች ወደ አልቃሾቹ በመጠጋት “ማልቀስ ተገቢ አለመሆኑን፣ ፈጣሪን ማስቀየም እንደሆነ” በመግለፅ ከለቅሶው እንዲታቀቡ ይገስጿቸዋል፡፡ ልጇ የሞተባትንም ሴት ነጠል በማድረግ ካፅናኗት በኋላ መሀል አናቷን ቅቤ በመቀባት “ፈጣሪ ከዚህ የተሻለ፤ የሚያድግ ልጅ” በቅርብ እንደሚሰጣት በማግባባት የለቅሶው ፍፃሜ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡
ህፃኑ የሞተው ጀንበር ከመጥለቋ ቀደም ብሎ ከሆነ በአካባቢው ካሉ ወንዶች ጠንከር ያሉት እና ልምዱ ያላቸው ተለይተው ለቀብር ይሆናል ተብሎ የተመረጠውን ከሰፈሩ ወጣ ብሎ የሚገኝን ዛፍ ለመቦርቦር የሚያስችሉ እንደ ገጀራ፣ መጥረቢያ፣ ፋስ እና ገሶ የመሳሰሉ መሳሪያዎችን በመያዝ በፍጥነት እቦታው ደርሰው ሰው እና አውሬ በቀላሉ ሊደርስ ከማይችልበት ስፍራ ላይ በመሰላል በመውጣት ዛፉን የሳጥን ቅርፅ አስይዘው ይቦረቡራሉ፡፡ የሚመረጠው ዛፍ ቢያንስ የሁለት ሰው እቅፍ የሚሞላ፣ በንፋስ ይወድቃል ተብሎ የማይገመት እና በቀላሉ መቦርቦር የሚችል “ካራሾ” ወይም “ዲኦ”/ዋንዛ/ የሚባል ዛፍ ነው፡፡
ለአዋቂዎች የሚደረግ የለቅሶ ስርዓት፦
በሸካቾ ብሔረሰብ ባህል መሰረት በዕድሜ ገፋ ላሉ ሰዎች የሚደረግ የለቅሶ ስርዓት ልዩነት የሚኖረው ሟች ወይም የሟች ቤተሰቦች ባላቸው ኢኮኖሚያዊ አቅም፣ በማህበረሰቡ ዘንድ እንዳላቸው ተቀባይነት እና ሟች የባህላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም ማለት ሟች በህይወት ዘመኑ ያከማቸው ሀብትና ንብረት ያለው ከሆነ የለቅሶ ስርዓቱ የዚያኑ ያህል በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ያልፋል፡፡ ነገር ግን የሟች የኢኮኖሚ አቅም ዝቅተኛ ከሆነ እምብዛም የደመቀ ለቅሶ እና ሰፋ ያለ ስርዓት ላይኖር ይችላል፡፡ በሌላ አንፃርም ሟች በህይወት ዘመኑ ከማህበረሰቡ ጋር የነበረው መስተጋብር ዝቅተኛ ከሆነ በዚያው መጠን የለቅሶ ስርዓቱ ሊደበዝዝ ይችላል፡፡
የሸካቾ ብሔረሰብ እንደአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ የራሱ በሆነ ንጉስ የሚመራ ነበር፡፡ በዚህ የንግስና ስርዓት ውስጥ በተዋረድ ካሉ የባህላዊ ስልጣን ባለቤቶች መካከል አንዱ ቢሞት የለቅሶ ስርዓቱ “ከተራው” የህብረተሰብ ክፍል የለቅሶ ስርዓት የሚለይበት የራሱ የሆነ ገፅታ ያለው ቢሆንም ያን ያህል ጉልህ ነው ተብሎ የሚገለፅ ልዩነት አይስተዋልም፡፡
ህመምተኛው ያለበት ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን በእድሜ ከፍ ያሉ የታማሚው ዘመዶች እና የአካባቢው ሽማግሌዎች እንደተረዱ በዚህ ወቅት የሚፈፀመውን ሌላኛውን ተግባር “በሽተኛው አንደበቱ ከመዘጋቱ በፊት ሀብት እና ንብረቱ እንዴት እንዲሆንለት እንደሚፈልግ ለማወቅ በቤተሰቡ አባላት የጋራ ስምምነት ለተመረጡ ሦስት ሽማግሌዎች እንዲናዘዝ ይደረጋል፡፡ ዛሬ ዛሬ ኑዛዜውን መፃፍ የሚችል አንድ ሰው ከሽማግሌዎቹ ጋር አብሮ እንዲሆን የሚደረግ ቢሆንም ቀደም ባለው ጊዜ ግን ሽማግሌዎቹ የሰሙትን በቃል እንዲያስተላልፉ ነበር የሚደረገው፡፡
የታማሚው ነፍስ ማለፏ ከጎን ባሉ የዕድሜ ባለፀጎች እንደተረጋገጠ ወዲያውኑ የሟችን ታላቅ ወንድ ልጅ በማስጠራት (ወንድ ልጅ የሌላቸው ከሆነ ከቤተሰቡ መካከል የቅርብ ዘመድ የሆነ ታላቅ ወንድ ሊሆን ይችላል) ስለ ሁኔታው አስረድተው አስክሬኑን እንዲያጥብ ያደርጉታል፡፡ ከዚያም ሽማግሌዎቹ ወዲያውኑ የግንዘቱን ተግባር ይፈፅማሉ፡፡ አስክሬኑን ቀጥ አድርጎ በጀርባው በማስተኛት አይኑን እንዲሸፈን፣ ጥርሶቹ እንዲከደኑ፣ ከንፈሩ እንዲገጠም ካደረጉ በኋላ ሁለት እጆቹ ብልቱን እንዲሸፍኑ አድርገው የእግሮቹን አውራ ጣቶች እና ጉልበት አጣምረው በቃጫ ያስራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ አድርገው ሬሳውን ከመከፈናቸው


በፊት በዕድሜ ፀና ያሉ የሟች ቤተሰቦችን ወደ ሬሳ ቤቱ እንዲቀርቡ በማስደረግ ሬሳውን ወደ በረንዳ አውጥተው ሞቱን እንዲያረጋግጡ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ድምፅ ጎላ ብሎ እንዳይወጣ የሚከለከል ቢሆንም የሚኖረው ለቅሶ መሪር ነው፡፡በመቀጠልም ለዚሁ ተግባር በተዘጋጀ ትልቅ ጋቢ አስከሬኑን ከፍነው በሳጥን ውስጥ በማስገባት የክዳኑን ዙሪያ በሚስማር በመምታት ምንም አይነት ክፍተት እንዳይኖር ያደርጋሉ፡፡
ሬሳ ክፍል ውስጥ የሚገኙት ሽማግሌዎች እና አስተናባሪዎች የሳጥኑን ክዳን ዙሪያ ሰም እያቀለጡ በአግባቡ የመሸፈን ስራ ሲሰሩ ከደጅ ያሉት ትልቅ በሬ አርደው ቆዳውን ለሬሳ ሳጥኑ መሸፈኛ እንዲሆን ያቀርባሉ፡፡ ሽማግሌዎችም ሳጥኑን በቀረበላቸው ትኩስ ቆዳ በመሸፈን ይጠፍራሉ፡፡ በመጨረሻም የተጠፈረበትን ዙሪያ ገባ ሰም አፍስሶ በመሸፈን በሬሳ ክፍል ውስጥ እሳት ዳር በእንጨት ፍርግርግ ተሰርቶ በተዘጋጀ የሬሳ ሳጥን ማስቀመጫ ላይ ሬሳውን በማኖር ጥሩ መዓዛ ያላቸው የጭስ እንጨቶች በብዛት እንዲጨሱ ይደረጋል፡፡ መልካም ጠረን አላቸው ተብለው ከሚመረጡት መካከል ጤናዳም፣ የነጭ ባህር ዛፍ ቅጠል፣ አሪቲ፣ ኮሰረት እና የወይራ እንጨት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ጤናዳም እና የነጭ ባህር ዛፍ ቅጠል ሬሳውን ለማጠብም ይገለገሉባቸዋል፡፡ ይህ ተግባር ጥርስ ካላበቀሉ ህፃናት ውጭ ላሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሟች ሴት ከሆነች የእጥበቱን ስራ የምታከናውነው የመጀመሪያዋ ሴት ልጅ ነች፤ ሟች ሴት ልጅ የሌላቸው ከሆነ የታላቅ ወንድ ልጅ ሚስት እጥበቱን እንድታከናውን ይደረጋል፡፡
በሸካቾ ብሔረሰብ ባህላዊ የለቅሶ ስርዓት ወቅት ሰፊውን ድርሻ የሚይዙት ከቀብር በፊት የሚፈፀሙ ዝግጅቶች ናቸው፡፡ ይህ ዝግጅት ሟች አንዳች ማህበራዊ ስልጣን ወይም ኢኮኖሚያዊ አቅም ያለው ከሆነ ደግሞ ከሌላው ይልቅ ሰፋ ይላል፡፡ ከቀብር በፊት ከሚከናወኑ ዝግጅቶች መካከል የምግብ እና መጠጥ ዝግጅት፣ ለቅሶ ነጋሪዎችን ማሰናዳት፣ በሟች ማሳ መፈፀም ያለባቸውን ተግባራት ማከናወን፣ ለእርድ የሚሆኑ ከብቶች ማዘጋጀት፣ የቀብር መሄጃውን ማፅዳት እና የቀብሩን ቦታና ቤት ማዘጋጀት፣ የመኖሪያ ቤቱን አካባቢ ማፅዳት እና ዳስ መስራት፣ አስክሬኑ ተሸፍኖ የሚሄድበት ሰረገላ ማዘጋጀት፣ በቀብሩ ወቅት አገልግሎት ላይ የሚውሉ አልባሳትን እና ቁሳቁሶችን ማዘጋጀት፣. . .ወዘተ የሚሉት ዋነኛውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡
የምግብ እና መጠጥ ዝግጅት፦
የሸካቾ ብሔረሰብ ባህላዊ ምግብ የሚባለው ቆጮ ሲሆን ጠጅ ወይም ቦርዴ ደግሞ በብሔረሰቡ በግንባር ቀደምትነት የሚመረጡ ባህላዊ መጠጦች ናቸው፡፡ ቆጮ በብሔረሰቡ ዘንድ በበዓላት ቀን አሊያም ለየት ባሉ ዝግጅቶች ላይ ብቻ ለምግብነት የሚውል የምግብ ዓይነት ሳይሆን ሁሌም ከጠዋት እስከ ማታ ከሌሎች ማባያዎች ጋር ለምግብነት የሚውል ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን በከተሞች አልፎ አልፎም ለከተሞች አቅራቢያ በሆኑ የገጠር ክፍሎችም ዘንድ እንጀራም እንደ አማራጭ በማዕዱ ላይ ይቀርባል፡፡
በአንድ የለቅሶ ስርዓት ላይ በዋናነት የሚቀርብ የምግብ ዓይነት እንደመሆኑ መጠን በቀብሩ ዕለት ሊገኝ ይችላል ተብሎ እንደሚገመተው ሰው ቁጥር ልክ ቆጮን በብዛት እና በጥራት ለማዘጋጀት የሚያስችልን ቀን ከግምት ውስጥ አስገብቶ የቀብር ጊዜን መወሰን በብሔረሰቡ ዘንድ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ቆጮው የሚዘጋጀው ሞት በተከሰተበት አካባቢ ባሉት ሴቶች እና በሩቅም ባሉ የሟች ጎሳ አባል በሆኑ ሰዎች ቤትም ጭምር ነው፡፡ በብሔረሰቡ ዘንድ ለቆጮ ማባያነት የበሬ ወይም የበግ ስጋ፣ ጎመን እና አይብ ተመራጮች ናቸው፡፡
በቀብሩ ዕለት ከተለያዩ አካባቢዎች ለሚመጡ ለቀስተኞች ከቀብር በኋላ ከሚቀርቡ ባህላዊ መጠጦች መካከል ለዝግጅት ከወር በላይ የሚፈልገው ጠጅ (ጠጅ በሸክኛ “ቢቶ” የሚባል ሲሆን በዕውቅ ባለሙያ ከወር እስከ ሦስት ወር ድረስ እንዲቆይ ተደርጎ የሚዘጋጀው ግን “ቢታ ቢቶ” ይሰኛል፤ ከጠጅም ጠጅ እንደማለት) ዋነኛውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በዋናነት ጠጅ የሚዘጋጀው ከማር እና ከጌሾ ሲሆን ዝግጅቱ የሚካሔደው በዋናነት በሟች ቤት ውስጥ ሆኖ በአካባቢው ያሉ በጠጅ መጥመቅ ስራቸው የተካኑ ሴቶች አስተባባሪነት ነው፡፡ ጠጁ ተጥሎ አንድ ወር ከቆየ በኋለ ዳግም በማርና በውኃ በመበጥበጥ ለሌሎች በርካታ ቀናት የሚቆይበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡ ይህ ሲሆን ጠጁ ከአስካሪነቱ ይልቅ ለሰውነት የሚሰጠው ጠቀሜታ ይጨምራል ተብሎ ይታመናል፡፡ ከጠጅ በተጨማሪ ከቀይ ጤፍ የሚዘጋጀው “ቦርዴ”ም ከቀብር በኋላ በአማራጭነት የሚቀርብ በመሆኑ በዚሁ ወቅት የሚዘጋጅ ነው፡፡
ሌላው በቀብር ዕለት ለምግብነት ለሚቀርበው ቆሎ እና ንፍሮ ዝግጅት የሚሆን በቆሎ እና ባቄላ፣ ቡና እና ለጬሞ ዝግጅት የሚሆን የቡና ቅጠል ማሰናዳት በቅድመ ቀብር ወቅት ከሚፈፀሙ የምግብ እና የመጠጥ ዝግጅቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በሸካቾ ብሔረሰብ ባህል መሰረት የብሔረሰቡ አባል ሆኖ ለቅሶ አለመድረስ ከህብረተሰቡ ጋር ከሚያቃቅሩ ጉዳዮች መካከል በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ በመሆኑም ሞት በተከሰተበት አካባቢ ያሉት አዛውንቶች ከቤተሰቡ አባላት ጋር በመሰብሰብ የቀብሩን ቀን እና በቀብሩ ዕለት በዋናነት እንዲገኙ የሚፈልጓቸውን ሰዎች ዝርዝር በጋራ ተነጋግረው ይወስናሉ፡፡ ቀደም ባለው የብሔረሰቡ እምነት መሰረት የቀብር ቀን ሰኞ፣ ረቡዕ እና ዓርብ ላይ እንዲውል አይደረግም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ቀናት እህል ቢዘራባቸው እንኳ አያበቅሉም፤ ደረቅ ናቸው ተብሎ የሚታመን ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ ድርሻ የሚሰጣቸው የህብረተሰቡ አካላት ሲሞቱ የብሔረሰቡ አባላት ወደሚኖሩባቸው የተለያዩ አካባቢዎች በሙሉ መልዕክተኞችን በእግር፣ በፈረስ እና በመኪና በመላክ የቀብሩን ቀን እና ቦታ በአግባቡ ተናግረው እንዲመለሱ ይደረጋል፡፡
ለመልዕክተኛነት የሚመረጡት ሰዎች ጎልማሳ ሆነው የጤንነታቸው ሁኔታ “መልዕክቱን ሳያደርሱ ከመንገድ ሊቀሩ ይችላሉ” የሚል ስጋት ውስጥ የማይከቱ እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሚላኩበትን አካባቢ እና ሰው የሚያውቁ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ ይህ ምርጫ የቤተሰቡ አባላት የሆኑ ጎልማሶችን አያካትትም፡፡ ምክንያቱም እነሱ በሐዘን ተጎድተዋል በሚል ነው፡፡ በዚህ መልክ ተመልምለው የተላኩት መልዕክተኞች ወደተላኩበት ሰው ቤት እንደደረሱ በአካባቢው ከሚገኙ ሰዎች ቤቱ በእርግጥ የተላኩበት ሰው መሆኑን፤አለመቀየሩን በማጣራት በቀስታ ወደ ውስጥ ዘልቀው ሟቹ የሚስት ዘመድ ከሆነ ለባል፣ የባል ዘመድ ከሆነ ደግሞ ለሚስት ስለሁኔታው ቀድመው በማስረዳት ለሟች ወገን በማስተዛዘን እና በቀስታ በመንገር ይላቀሳሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ትንሽ ዕረፍት እንዳደረጉ የቀብሩን ቀን እና ቦታ በጥንቃቄ ነግረው ሌሎች በአካባቢው ለሚገኙ የብሔረሰቡ አባላት ንገሩ መባላቸውን በማሳሰብ የሄዱበት መንገድ ሩቅ ከሆነ እንደሁኔታው አንድም ሆነ ሁለት ቀን አርፈው ይመለሳሉ፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ታልፎ መልዕክቱ ከደረሰው በኋላ ብዙም አጥጋቢ ባልሆነ ምክንያት በቀብሩ ዕለት በማይገኝ የብሔረሰቡ አባል ላይ የሚኖረው መገለል ከፍተኛ ነው፡፡
የሰው ልጅ ታሞ አልጋ የሚይዝበት ብሎም የሚሞትበት ቀን በውል የማይታወቅ በመሆኑ አንድ ሰው በሚሞትበት ወቅት በጅምር የሚቀሩ ስራዎች፣ ያልተፈፀሙ ዕቅዶች፣ ያልተከፈሉ ዕዳዎች ወይም ያልተመለሱ ብድሮች ይኖራሉ፡፡ የሸካቾ ብሔረሰብ በዋናነት የሚተዳደረው በግብርና ስራ ላይ እንደመሆኑ መጠን በአካባቢው የሚሰሩ ስራዎች ወቅትን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ በመሆኑም ጊዜው የእርሻ ሆኖ ሳለ በተለያዩ ምክንያቶች የሟች ማሳ ጦሙን ያደረ ከሆነ በአካባቢው የሚገኙ የጎሳው አባላት ተሰባስበው በመካከከር የሟችን ማሳ መንጥረው፣ አርሰው፣ ጎልጉለው እና ዘርተው ከቀብር በፊት በማሰናዳት ሟች ወገን ያለው መሆኑን ማስመስከር የተለመደ ተግባር ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሟችን ማሳዎች ማጠር፣ ቀፎ መስቀል እና ቆጮውን መኮትኮትም በእነዚሁ አካላት በተጓዳኝ ይፈፀማል፡፡ ከዚህ ጋር በተጓዳኝ በሌሎች አካላትም ጭምር የሚከወነው ሌላው ተግባር ለማገዶ የሚሆን እንጨት ማሰናዳት ነው፡፡ ሞት በአካባቢው መከሰቱን የሰሙ በአካባቢው የሚገኙ አባወራዎች በሙሉ ከቀብሩ ቀን ቀደም ብለው በነፍስ ወከፍ አንዳንድ እንጨት በመያዝ በሟች ቤት እያመጡ መከመር የኖረ ልምድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን ማሳውን በማሰናዳት ላይ የሚገኙት አካላት በማሳው ውስጥ የሚገኙ ደረቅ ዛፎችን በመጣል በህብረት ፈልጠው በማሳ ያለው ስራ እስኪጠናቀቅ ወደ ሟች ቤት በማጓዝ የማገዶ እንጨት ችግርን ይቀርፋሉ፡፡ በሸካቾዎች ባህል ለወትሮውም ቢሆን የማገዶ እንጨት የማቅረብ ግዴታ የተጣለው በወንዱ ላይ ነው፡፡
የቀብሩ ዕለት ከተለያዩ አካባቢዎች ተሰባስበው የመጡት ለቀስተኞች የተሻለ ነገር ተመግበው እንዲሄዱ ማድረግ በሸካቾዎች ባህል የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ስለሆነም የሟች ቤተሰቦች፣ አማቾች እና የጎሳው አባላት በዋናነት ለዚህ የሚሆኑ ግብዓቶችን የማሟላት ማህበራዊ ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡በመሆኑም የሟችን ልጅ ያገቡ አቅማቸው የሚፈቅድ ከሆነ እያንዳንዳቸው አንዳንድ በሬ ወይም መስና ከብት፣ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑት ደግሞ ሙክት በግ፣ ቅርበት ያላቸው የሟች ጎሳ አባላት እና ጓደኞች ደግሞ አቅማቸው በፈቀደ መጠን ከፍ ሲል ከተጠቀሱት አንዱን መርጠው በማቅረብ የሟች ቤተሰቦች ባዘጋጁት ላይ ተጨማሪ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
የቀብር ቦታ በሸክኛ “ጌዳሜ ጣኦ” የሚባል ሲሆን ቀደም ባለው የሸካቾዎች ባህል መሰረት በሁለት የተለያዩ ስፍራዎች ላይ የቀብር ቦታ እንዲዘጋጅ ይመረጣል፡፡ አንደኛው በሟች መኖሪያ አካባቢ ባለ የግል ማሳ ውስጥ የሚሰናዳ ነው፡፡ ሟች በማሳው ውስጥ የሚቀበርበት ምክንያቶች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው በኑዛዜው ወቅት ሟች “በማሳዬ ውስጥ ቅበሩኝ” ያለ እንደሆነ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የሟች ቤተሰቦች በአቅራቢያችን ተቀብሮ መቃብሩን በየጊዜው እየጎበኘን መንከባከብ እንፈልጋለን የሚል ሀሳብ ያቀረቡ እንደሆነ ነው፡፡
ሁለተኛው የቀብር ስፍራ ከአካባቢው ወጣ ብሎ በሚገኝ ኮረብታማ ስፍራ ላይ የአካባቢው ሰዎች በጋራ ያሰናዱት የቀብር ስፍራ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በእንዲህ ያለ ስፍራ የሚቀበሩት ነገስታት፣ የጎሳ መሪዎች፣ ቃልቻዎች እና በማህበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ስም ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም በቀብሩ ዕለት ሴቶች ለቀብር በተከለለው አጥቢያ ውስጥ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም፡፡ ይህ የሚሆነውም ቦታው ንፁኃን ያረፉበት የተቀደሰ ስፍራ ተደርጎ ስለሚታሰብ ምናልባት ቀናቸው ላይ የሆኑ ሴቶች ተቀላቅለው ገብተው ያረክሱታል ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡
እነዚህ የቀብር ስፍራዎች በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ ቀርተዋል ለማለት ባያስደፍርም አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በየኃይማኖት ስፍራው ተከልሎ በሚገኘው የቀብር ቦታ መቅበርን ተቀዳሚ ምርጫው ያደርጋል፡፡ የሆነ ሆኖ ባህላዊውን የቀብር ስፍራ አዘገጃጀት ስንመለከት የቀብሩ ዕለት ሦስት ቀን ሲቀረው ወደ ቀብር ስፍራ መሄጃ መንገዱን ሰፋ አድርጎ መመንጠር ቀዳሚው ተግባር ነው፡፡ ቀጥሎም ልምዱ ያላቸው ሰዎች ተለይተው ቀብሩ እዚህ ጋር ቢሆን የተሻለ ይሆናል የሚሉትን ቦታ በመምረጥ በአራት ማዕዘን ቅርፅ አራት ክንድ ጥልቀት ያለው ጉርጓድ ሰፋ አድርገው ይቆፍራሉ፡፡ ከዚያም የሬሳ ሳጥኑ የሚያርፍበትን ዙሪያ ገባ በሙሉ ድንጋይ በሸክላ አፈር እያጣበቁ (በአሁኑ ጊዜ በሲሚንቶ ነው የሚያጣብቁት) በጥንቃቄ ይደረድራሉ፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የመኖሪያ ቤቱን አካባቢ የማፅዳት ኃላፊነት የሚጣለው በወጣት ሴቶች እና ወንዶች ላይ ነው፡፡ ይህን “ሴቶቹ የመኖሪያ ቤቱን አካባቢ “ጊጠሮ” በሚባል በሁለት በኩል መያዣ ባለው የተቆለመመ ገጀራ መሰል ብረት በመታገዝ ሙልጭ አድርገው ሳርና ቆሻሻውን የማስወገድ ተግባራቸውን ሲወጡ ወንዶቹ ደግሞ ከሴቶቹ አቅም በላይ የሚሆነውን በገጀራ በመመንጠር እና በቤቱ ዙሪያ ያለውን አጥር የማጠናከር ድርሻቸውን በትብብር ያከናውናሉ፡፡ “ሌላው በጎልማሶች የሚሰራው ተግባር የዳስ ስራ ነው፡፡ ዳሱ የሚጣለው በሟች መኖሪያ ቤት አራቱም አቅጣጫ ነው፡፡
ከአራቱም አቅጣጫ የሚመጡትን ለቀስተኞች በየመጡበት አቅጣጫ ተቀብሎ ለማስተናገድ ሲሆን በአራቱም ዳስ ውስጥ በሚመደቡት አስር አስር አስተባባሪዎች አማካኝነት “ማን መጥቷል ? ማንስ አልመጣም ?” የሚለውን በአግባቡ ለመለየትም ጭምር ነው፡፡ በእያንዳንዱ ዳስ ውስጥ በዋናነት የሚመደቡት 5 ወንድ እና 5 ሴት አስተናጋጆች ሲሆኑ ከሴቱም ከወንዱም አንዳንድ አስተባባሪ ይሰየማል፡፡ እነዚህ አካላት ከቀብሩ አንድ ቀን ቀደም ብለው በመሰባሰብ በያቅጣጫቸው ያሉ ቀበሌዎችን በአግባቡ መለየት፣ ማን ተቀብሎ ቦታ ያስይዝ፣ ማን ምግብ ያቅርብ፣ ማንስ መጠጥ ያሳልፍ፣ . . .ወዘተ የሚሉት ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ነው የሚያድሩት፡፡ በመሆኑም የእነዚህ አካላት ምርጫ በህብረተሰቡ ዘንድ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈፀም ነው፡፡ ለዳስ መስሪያ በዋናነት ከሚያስፈልጉት ግብዓቶች መካከል በርከት ያለ የቀርቀሀ እንጨት፣ የቆጮ ቅጠል እና ሀረግ (ቃጫ) ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ሞት በተከሰተበት አካባቢ የሚገኙ የአካባቢው ሰዎች እና የቤተሰቡ አባላት ቀብሩ 5 ቀን ሲቀረው ጀምረው ያዘጋጇቸውን የዳስ መስሪያ ቁሳቁሶች ተጠቅመው በየአቅጣጫው በመከፋፈል ከቀብሩ ዕለት ሦስት ቀን ቀደም ብለው የዳሱን ስራ በህብረት ይሰራሉ፡፡ አካባቢው 13ቱንም ወር ሙሉ ዝናብ የማያጣው በመሆኑ በክዳንነት የሚያገለግለውን የቆጮ ቅጠል በርከት አድርጎ ማልበስ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ በተለይም ሟች ንጉስ አሊያም የጎሳ መሪ ከሆነ በዕለቱ ከባድ ዝናብ ይጥላል ተብሎ የሚታመን በመሆኑ በእነዚህ አካላት ለቅሶ ላይ የሚዘጋጁ ዳሶች ከወትሮው የተሻለ ጥንቃቄ ይደረግባቸዋል፡፡
በዚህ መልክ በሚዘጋጀው ዳስ ውስጥ የሟች አማቾች በመጡበት ቀበሌ አቅጣጫ በተሰራው ውስጥ የቀብሩ ዕለትም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት የሀዘን ቀናት እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡ የአማቾቹ ቁጥር ከዳሱ ቁጥር የሚበልጥ ከሆነ ደግሞ እንደሁኔታው በጋራ እንዲቀመጡ የሚደረግ ይሆናል፡፡
አስክሬን ታጅቦ የሚሄድበት ሰረገላ ማዘጋጀት፦
ይህ ዝግጅት የሚከናወነው ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሳይሆን ንጉስ የሞተ ዕለት ብቻ ነው፡፡ አገልግሎቱም የንጉሱን አስክሬን ከሌላው ለቀስተኛ ለየት አድርጎ በክብር ከመቃብር ቦታው ድረስ ሸፍኖ ማድረስ ነው፡፡
ሰረገላው የሚዘጋጀው በቀርቀሀ ሆኖ የቤት ቅርፅ እንዲይዝ ተደርጎ ነው፡፡ አንዱን ቀርቀሀ ከሌላኛው በሀረግ እና በቃጫ በአግባቡ ካሰሩ በኋላ ደማቅ ከለር ባላቸው ጨርቆች እንዲሸፈን ይደረጋል፡፡ አስክሬኑ በሰረገላው ውስጥ ሆኖ የሚጓዝ ከመሆኑ አንፃር በሰረገላው ዝግጅት ወቅት ታሳቢ ከሚደረጉ ነገሮች መካከል አስክሬኑን በፍርርቅ ተሸክመው የሚጓዙ ከ20 የማያንሱ ሰዎችን በአግባቡ ሊይዝ የሚችል መሆኑ ነው፡፡
በዚህ መልክ የተዘጋጀው ሰረገላ በአራቱም ማዕዘን ከውጭ ሆነው በመተጋገዝ እንዲይዙ በተመረጡ ጠንከር ያሉ ሰዎች ትከሻ ላይ አርፎ በአዝግሞ እንዲጓዝ ይሆናል፡፡ ከውስጥ አስክሬኑን የተሸከሙት ሰዎች ከውጭ ባሉት ሰረገላ ተሸካሚዎች የእንቅስቃሴ ልክ አረማመዳቸውን በማስተካከል እየተጓዙ ከቀብር ስፍራው ይደርሳሉ፡፡
በሸካቾ ብሔረሰብ ለቅሶ ማህበራዊ ትስስርን ማጠንከሪያ፣ የሟችን እና የሟች ወገኖችን ማንነት መግለጫ፣ የሀብት መጠን ማሳወቂያ፣ ወዳጅ እና ጠላት መለያ፣. . .ወዘተ ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ በተለይም በቀብሩ ዕለት የሚኖረው ዝግጅት ደመቅ ያለ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው ከሟች ወይም ከሟች ቤተሰቦች ጋር ትውውቅ ያለው እያንዳንዱ የብሔረሰቡ አባል የትኛውንም አማራጭ ተጠቅሞ በቀብሩ ዕለት የመገኘት ማህበራዊ ግዴታ ያለበት መሆኑን አምኖ የተቀበለ በመሆኑ በቀብሩ ዕለት የሚገኘው ለቀስተኛ ቁጥር በእጅጉ የበዛ ነው፡፡ ይህ ሀቅ ይበልጡን የሚጎላው ደግሞ ሟች አንድ አይነት ባህላዊ የስልጣን ባለቤት ወይም ታዋቂ ግለሰብ የሆነ እንደሆነ ነው ፡፡
የቀብሩ ዕለት ጠዋት፤ ወፍ ከመንጫጫቱ አስቀድሞ በሟች ቤት አቅራቢያ በየአቅጣጫው በሚገኙ ኮረብታማ ቦታዎች ላይ በመሆን ጥሩንባ በተደጋጋሚ እንዲነፋ ይደረጋል፡፡ ይህን የሰሙ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ከተለያየ አካባቢ የተሰባሰቡት ለቀስተኞች ወዲያው ነቅተው ወደ ሟች ቤት ጉዟቸውን ያደርጋሉ፡፡ የሟች ቤተሰቦችም ከዚህን ሰዓት ጀምረው በዕለቱ መረር ያለ ለቅሶ እያደረጉ ከለቀስተኛው ፊት ይገኛሉ፡፡ የሚመጡትም ለቀስተኞች እንደቅርበታቸው ልክ ከሰፈር ጀምረው ከፍ ባለ ድምፅ ያለቅሳሉ፣ ደረታቸውን በሁለቱም እጆቻቸው አምርረው ይደቃሉ፣ እየዘለሉ ይወድቃሉ – ይነሳሉ፣ ፀጉራቸውን ይነጫሉ፣. . .ወዘተ፡፡ በዚህ መልክ የተጀመረው ለቅሶ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ያለማቋረጥ በደማቅ ሁኔታ ይቀጥላል፤ የመጣው ለቀስተኛ ሁሉ በከባድ የሀዘን ድባብ ውስጥ ሆነው ከሚያለቅሱት፣ እየወደቁ ከሚነሱት፣ ደረታቸውን በኃይል ከሚደቁት፣ ፊታቸውን ከሚቧጥጡት፣. . .የሟች ቤተዘመዶች ፊት ሲደርስ ከደጅ ጀምሮት የነበረውን ለቅሶ በማጠናከር የሚሆኑትን ሁሉ እየሆነ ሀዘናቸው ሀዘኑ፤ ጉዳታቸው ጉዳቱ መሆኑን ለማስመስከር ይጥራል፡፡
በዚህ ሁኔታ ተጀምሮ ያለማቋረጥ እስከ እኩለ ቀን ድረስ የቀጠለው ለቅሶ ይበልጥ የሚፋፋመው አስክሬኑ ከቤት ወጥቶ ጉዞ ሊጀምር ሲል ነው፡፡ በዚህ ጊዜ አብዛኛው የህብረተሰቡ አባል መረር ያለ ለቅሶ ያለቅሳል፡፡ ሴት የሟች ቤተሰቦች (በተለይም የሟች እናት፣ ሚስት እና ሴት ልጆች) የመውደቅ የመነሳታቸው ሁኔታ ከሌላው ጊዜ ያይላል፡፡ የሟች ሚስት፣ እናት እና እህቶች በወቅቱ ከሚለብሱት ጥቁር ልብስ ላይ ጣል የሚያደርጉት ከቃጫ የተሰራ “ፉሶ” የተሰኘ ነጭ ካባ መሰል ባህላዊ የሀዘን መግለጫ ይለብሳሉ፡፡

በባህሉ መሰረት ሬሳው ከቤት ወጥቶ ጉዞ ሲጀምር የሚከናወኑ ልዩ ልዩ ስርዓቶች የሚከናወኑ ይሆናል፡፡
መውደቅ –መነሳት ( (ቤኖ)፦
በሸካቾ ብሔረሰብ ባህላዊ የለቅሶ ስርዓት ላይ ዛሬም ድረስ በዋናነት ከሚፈፀሙት ባህላዊ ተግባራት መካከል ድምፅን ከፍ አድርጎ እያለቀሱ በተደጋጋሚ እየወደቁ መነሳት ነው፡፡ ይህን ተግባር በዋናነት የሚፈፅሙት ሴት የሟች ቤተሰቦች እና የቅርብ ወዳጆች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሀዘኑ እጅግ የጎዳቸው ወንዶችም ወድቀው ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ሴቶቹ በሚወድቁ በሚነሱበት ሰዓት ደረታቸውን በእጅጉ እየደቁ፣ ፊታቸውን እየቧጠጡ እና ፀጉራቸውን እየነጩ ነው፡፡ ይህንን የሚያደርጉት በዋናነት በተፈጠረው ክፉ አጋጣሚ እጅጉን ማዘናቸውን ለመግለፅ እና ከእሱ/ ከእሷ/ይልቅ እኔ ነኝ መሞት ያለብኝ የሚለውን ስሜት እንዲወክልላቸው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሀዘን ስሜታቸውን ለታዳሚው በማጋባት የወገናቸው ለቅሶ የደመቀ እንዲሆን የማድረግ ዓላማም አለው፡፡
መውደቅ መነሳቱ የሚከወነው ቦታ እየተመረጠ ሳይሆን ድንገት በተገኙበት ስፍራ ላይ ስለሚሆን በርካታ ሰዎች ከፍ ላለ ጉዳት የሚጋለጡባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ የሟች የቅርብ ዘመድ ሆነው ነፍሰ ጡር የሆነች ሴት ካለች፣ ህመምተኞች ቢኖሩ፣ እርጅና የተጫጫናቸው ከሆኑ ወድቀው እራሳቸውን ለጉዳት ከመዳረጋቸው በፊት ቀደም ተብሎ ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ሆነው በሚመደቡ ጠንከር ያሉ ሴቶች ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ እነዚህ ሴቶች እንዲጠብቋቸው የተመደቡባቸው አካላት የመውደቅ አዝማሚያ ሲያሳዩ ከኋላ ሆነው በፍጥነት ወገባቸውን በመያዝ ከአደጋ ሊታደጓቸው ይገባል፡፡
ሙሾ (ያሶ)፦
በሸካቾ ብሔረሰብ ከሴቶችም ሆነ ከወንዶች መካከል ተመርጠው ወዲያ ወዲህ እያሉ ሙሾ በመደርደር አልቅሰው የሚያስለቅሱ ሰዎች አሉ፡፡ ይህን በተመለከተ “ሙሾ አውራጆች በዋናነት የሚመረጡት ከቤተሰብ አሊያም ከቅርብ ዘመድ መካከል ልምድ ያላቸው ተለይተው ነው፡፡ የሙሾ ደርዳሪዎች (በሸክኛ ለሴት “ያሳቺ”፣ ለወንድ ደግሞ “ያሳቾ” ይባላል) ምርጫ ከቤተሰብ አባላት መካከል እንዲሆን የተፈለገበት ምክንያት ከሌላው ይልቅ የሀዘኑ ስሜት በዋናነት የጎዳቸው በመሆኑ የማስለቀስ አቅም ያለው ሙሾ መደርደር ይችላሉ ተብሎ ስለሚታመን ነው።
ሙሾ አውራጆቹ አብዛኛውን ጊዜ ሙሾ የሚደረድሩባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች “ሙሾ የሚደረደረው የሟችን ደግነት፣ ጀግንነት፣ ለሰው አሳቢነት፣. . .ወዘተ በተመለከተ እና የሞትን ጨካኝነት፣ ሞት የማይቀር፤ የሚገልም ሆነ የሚያድን ፈጣሪ መሆኑን፣. . .ወዘተ በሚዳስሱ ጉዳዮች ዙሪያ ነው፡፡
ባህላዊ የማፅናኛ ዘፈን (ጎሞ)፦
የ”ጎሞ”ን ምንነት በሸካቾ ብሔረሰብ ባህል መሰረት የሟች ወገኖች በመራር ሀዘን እራሳቸውን ለከፋ አደጋ አሳልፈው እንዳይሰጡ፣ ቀጣይ ህይወታቸው ሀዘን የበዛበት ሆኖ እንዳይቀር፣ ከሀዘን በተቃራኒ ደስታ መኖሩን ለማስገንዘብ፣. . .ወዘተ በቀብሩ ዕለት በስፋት የሚከወን ባህላዊ የማፅናኛ ዘፈን ነው፡፡ ጎሞ ፍፁም ተቃርኗዊ በሆነ መልኩ በለቅሶ ስርዓት ወቅት የሚከወን ባህላዊ የማፅናኛ ዘፈን ነው፡፡ ይህ ዘፈን የሚከወነው ለቀስተኞች ወንዱ በአንድ ወገን ሴቱም በሌላኛው ወገን ተቧድነው ክብ በመስራት የሟች ወገኖች ሊያፅናና የሚችል ዘፈን እየዘፈኑ ነው፡፡ የወንዶቹ ቡድን ጦር እና ጋሻ ይዞ፣ በከበሮ፣ በጡርንባ እና በክራር በመታገዝ ባህላዊ ዘፈኖቹን እየተቀኘ ደማቅ በሆነ አከዋወን ይወጣዋል፡፡
ሴቶቹም በፊናቸው ባህላዊ የሀዘን ልብስ ለብሰው በከበሮ እና በጭብጨባ ከታጀበው ባህላዊ የማፅናኛ ዘፈን ይታደማሉ፡፡ በወንዱም ሆነ በሴቱ የሚደራጀው ቡድን በርካታ ሲሆን በአንድ ቡድን ውስጥ እንደሁኔታው አስርም ሆነ ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ተቧድነው ሰልታዊ በሆነ መልኩ በሚቃኘው ጭበጨባ እየታገዙ ወደ ላይ ዘለል ዘለል እያሉ ነው የሚጨፍሩት፡፡ አንዳንዴም ተቧዳኞቹ ወንዶች ከሆኑ በአንድ እጃቸው ጦር ይዘው በሌላኛው እጃቸው እርስ በእርስ በመያያዝ ወዲያ – ወዲህ፣ ላይ – ታች እያሉ ሲጨፍሩ ቆይተው ዘፈኑን ሲቋጩ አንድ ላይ በእግራቸው መሬቱን በከበሮ ስልት ረግጠው ሲያርፉ የታዳሚን ቀልብ
ይማርካል፡፡ ሴቶቹ ደግሞ ከመያያዝ ይልቅ ክብ ሰርተው ደመቅ ባለ ጭብጨባ እና በከበሮ እየታገዙ በወንዶቹ ስልት ላይ ታች እያሉ ክብ እየሰሩ መጨፈርን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡
ይህንን ባህላዊ የማፅናኛ ዘፈን እና ጭፈራ ከሟች ቤተሰቦች፣ እርጅና አብዝቶ ከተጫናቸው አዛውንቶች እና በደዌ ከተያዙ ሰዎች በስተቀር ሁሉም በሚችለው ልክ እንዲጨፍር ይጠበቃል፡፡ ይህ እንዲሆን የተደረገበትም ምክንያት ለቀስተኛው እዚያ የተገኘው ሀዘንተኞችን ለማፅናናት በመሆኑ በባህሉ መሰረት ሁሉን አቀፍ ማፅናኛ ተደርጎ በሚቆጠረው ስርዓት ላይ በመዝፈን፣ በማጨብጨብ፣ ከበሮ በመምታት፣ ክራር በመጫወት፣ ጥሩንባ በመንፋት፣ ጦር በመስበቅ፣. . .ወዘተ የሚጠበቅበትን ማህበራዊ ግዴታ ሊወጣ ይገባል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ማለፍ ያልፈለገ ቢኖር ግን አንድም ከሟች ወይም ከሟች ወገኖች ጋር ከፍ ያለ ቅያሜ ያለው ተደርጎ ይቆጠራል፤ በሌላ መልኩም ለቅሶውን ካልደረሱት አካላት እኩል ሊቆጠርም ይችላል፡፡
የጎሞ ዘፈን እና ጭፈራው የሚጀምረው እኩለ ቀን ላይ አስክሬኑ ከቤት ወጥቶ ጉዞ ሲጅምር ታዳሚው ሁሉ ቀኑን ሙሉ ሲያለቅስ ከነበረው ይልቅ ከግማሽ ሰዓት በላይ አምርሮ ካለቀሰ በኋላ ነው፡፡ ለቅሶው በዚህ ሁኔታ መረር ብሎ መቀጠሉን ያስተዋሉት አዛውንቶች በየአልቃሾቹ መሀል እየዞሩ ያስቆሟቸዋል፡፡ ለቅሶው እንዳበቃ ወደ መቃብር ስፍራ በሚወስደው መንገድ ላይ አስቀድሞ ከተዘጋጀ ሜዳ ላይ ሲደርሱ የጎሞ ስርዓቱ ይጀምራል፡፡
የጎሞ ስርዓቱ የሚጀምረው ሟቹ ንጉስ፣ የጎሳ መሪ፣ አዳኝ፣ በተለያዩ ማህበራዊ መለኪያዎች ጀግና፣ ኑሮን በትግል አሸንፎ ሲኖር የነበረ፣. . .ወዘተ ከሆነ ጦር በቀኝ ጋሻ በግራ እጃቸው ይዘው ወዲያ ወዲህ እያሉ በመፎከር እና በመሸለል ሞትን በያዙት ባህላዊ መሳሪያ እያስፈራሩ ያሉ የሚመስሉ ሰዎች በሚከውኑት ትርዒት ነው፡፡
በዚህ መልክ የሚጀመረውን የጎሞ ስርዓት ለቀስተኛው ሁሉ አንድ በአንድ ክብ ሰርቶ መታደም ይጀምራል፡፡ በክዋኔው ሂደት ታዳሚው ሞት የተወጋ ያህል ከለቅሶ መልስ የፈገገ ፊት እያሳየ በጭብጨባ ያደምቀዋል፡፡ ለከዋኝነት የሚመረጡት በአካባቢው በጀግንነታቸው የተመሰከረላቸው ሰዎች ስለሚሆኑ ታዳሚው እግረ መንገዱን ለከዋኞቹ የጦር አሰባበቅ እና አፎካከር ሂደትም ድጋፉን ያሳያል፡፡
በዚህ ወቅት በባህላዊ ጌጦች ያሸበረቁ ፈረሶችን የያዙ ሰዎች ወደ ትርዒቱ በመቀላለቀል ፈረሶቹን ወዲያና ወዲህ እያንጎማለሉ ለሟች ጀግንነት ተጨማሪ ምስክርነታቸውን በድርጊት ይገልፃሉ፡፡ በመቀጠልም ክራር የያዙት ባህላዊ ዘፋኞች ቅኝታቸውን ማሰማት ይጀምራሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ታዳሚው ወዲያውኑ መቧደን ስለሚጀምር ባህላዊ ዘፋኞቹ በየቡድኑ አንዳንድ እየተዘሩ ክዋኔውን ማድመቅ ይጀምራሉ፡፡ ሴቶችም ለብቻቸው ተቧድነው በከበሮ እና በጭብጨባ በመታገዝ ደመቅ አድርገው እየጨፈሩ የሚጠበቅባቸውን ማህበራዊ ግዴታ መወጣት ይጀምራሉ፡፡
ሟች ሴት ከሆነች ከፍ ሲል ከተጠቀሱት የክዋኔ አይነቶች ጦር እና ጋሻ ይዘው የሚፎክሩት፣ ፈረስ አስጊጠው ላይ እና ታች የሚሉት ይቀርና በሴቶች ብቻ የሚከወን “ሸሬ የጦ” (ግማሽ አካሉ መሬት ውስጥ የተቀበረን ጋን በሰፌድ እየመቱ የመስበር ስርዓት) በተሰኘ ክዋኔ ይተካል፡፡ ይህን ተግባር የሟች የቅርብ ዘመድ የሆኑ እና “ከእጇ በልቻለሁ፣ ጠጥቻለሁ !” የሚሉ ሴቶች ክብ ሰርተው ቀደም ተብሎ የጎሞ ስርዓቱ በሚከናወንበት ቦታ ላይ የተዘጋጀን ጋን ባህላዊ የማፅናኛ ዘፈን ግጥሙን እየደረደሩ ተራ በተራ በያዙት ሰፌድ ጫፉን እየመቱ የጋኑን አፍ ይሰብራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በዙሪያቸው የተሰበሰቡ ሴቶች ከፍ ባለ ድምፅ እና በከበሮ ታጅበው የማፅናኛ ዘፈኑን በድምቀት ያወጡታል፡፡
አንድ ሴት ትዳር መስርታ የራሷን ኑሮ መምራት ከጀመረች በኋላ ስትሞት ከእጇ የበሉ እና የጠጡ ሴቶች ሀዘናቸውን የሚገልፁት እሷ በህይወት ሳለች ትጠቀምበት የነበረውን አንድ የጠጅ/የጠላ/ መጥመቂያ ጋን እየተቀባበሉ አፉን ሲሰብሩ ነው፡፡ ይህ የሚሆነውም ‘ሟች ለተቸገረ የምታበላ፣ የምታጠጣ ደግ እና ሙያተኛ ነበረች፣ ዛሬ ግን አፈር በላት’ የሚለውን ለማመላከት ሲሆን ከሌሎቹ ዕቃዎቿ ይልቅ ጋን የሚመረጠውም በአካባቢው ጠጅ በአግባቡ የመጣል ብቃት ከሙያዎች ሁሉ የሚሞገስ በመሆኑ ነው፡፡
በዚህ መልክ የተጀመረው ክዋኔ ለሁለት ሰዓት ያህል ያለሟቋረጥ ቀጥሎ በሽማግሌዎች በቃ ባይነት እንዲቆም ይደረጋል፡፡ ልክ የጎሞ ስርዓቱ እንዳበቃ ጉዞ ወደ ቀብር ስፍራ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ሟች አንድ አይነት ማህበራዊ ስልጣን ያለው ከሆነ ቀብሩ የሚፈፀመው ለእነዚህ አካላት ታስቦ በተዘጋጀ አካባቢ ስለሚሆን ሴቶች ወደ መካነ መቃብሩ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም፡፡ አሁን አሁን ግን “ሀዘናችን በአግባቡ የሚቆርጥልን ሲቀበር ስናይ ነው” በሚል ሴቶች ወደ ተከለከለው ስፍራ ባህላዊውን ደንብ ተላልፈው እየገቡ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው፡፡
ልክ የቀብር ቦታው ሲደርሱ ቀደም ሲል አስክሬኑ ከቤት ሲወጣ በነበረው ልክ አምርረው ማልቀስ ይጀምራሉ፡፡ የቀብር አፈፃፀም ሂደቱን በሚገባ የሚያውቁት አካላት አስክሬኑን ከመሸከሚያው አውርደው ወደ ተዘጋጀለት ጉድጓድ ውስጥ በጥንቃቄ የማስገባቱን ተግባር ይፈፅማሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ከቀደሙት ጊዜያት በበለጠ መልኩ ከፍ ባለ ድምፅ እና በምሬት ማልቀሱ፣ መውደቅ – መነሳቱ፣ ደረት መድቃቱ – ፊት መቧጠጡ፣ . . .ወዘተ በስፋት ይከወናል፡፡ ከሟች ጎሳ አባላት መካከል በዕድሜ ገፋ ያሉት አዛውንት የመጀመሪያውን አፈር ወደ አስክሬኑ በመጨመር አፈር የማልበሱን ሂደት ያስጀምራሉ፡፡ ወንዶቹ በመተጋገዝ አፈር በመጨመር ጉድጓዱን ከሞሉት በኋላ በስተመጨረሻ በድንጋይ ጥቅጥቅ አድርገው በመድፈን ግብዓተ መሬቱን ይፈፅማሉ፡፡
እያንዳንዱ ለቀስተኛ የመጣበትን አቅጣጫ መሰረት አድርጎ በተዘጋጀለት ሰፋ ያለ ዳስ ውስጥ በአስተባባሪዎች አማካይነት እጅ እና ፊቱን እየታጠበ እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ወዲያውኑ በእሳት ለብ ባለ የቆጮ ቅጠል የተሰራ ሰሀን መሰል ነገር ለእያንዳንዱ ይታደላል፡፡ ከዚያም በአስተናጋጆች አማካኝነት ገሚሱ ቆጮውን አስቀድሞ ሲያስይዝ ሌላዋ ወጥ ለእያንዳንዱ እያደረገች ታልፋለች፡፡ ተከታዩ አስተናጋጅ ደግሞ ከቀርቀሀ በተዘጋጀ “ዶሎ” በተሰኘ ባህላዊ መጠጫ ጠጅ/ ጠላ እየቀዳ ማደሉን ይያያዛል፡፡
በሸካቾ ባህል በሌሎች ዘንድ ‘ሰልስት’ በሚል የሚከበረው ስርዓት በአራተኛው ቀን በደማቅ ሁኔታ ነው የሚከበረው፡፡ በዚህ ቀን ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤት እና ጓደኞች ወፍ ሳይንጫጫ ከያሉበት በሟች ቤት ተሰባስበው ወንዶች ጦር፣ ሴቶች ደግሞ የቆጮ መቁረጫ ቢላቸውን በመያዝ ወደ ቀብሩ ስፍራ ይጓዛሉ፡፡ እዚያ እንደደረሱም ሁሉም ከ30 ደቂቃ ላላነሰ ጊዜ በጣም አልቅሰው ሴቶች በያዙት ቢላዋ በአቅራቢያቸው ካለ ቆጮ ቅጠል እየቆራረጡ፣ ወንዶቹ ደግሞ በጦራቸው መሬት እየወጉ በጋራ `ደፒዮ – ዳፒዮ ኤሳቤ’ (ከዚህ በኋላ ሞት እኛን መግደሉን ያቁም፣ ሞት በዚሁ ይብቃ !) በማለት ለቅሶዋቸውን ያሳርጋሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ሀዘንተኛው ሁሉ እጁን እና ፊቱን ታጥቦ በሟች ቤት የተዘጋጀውን ምግብ በመቅመስ ሀዘኑን ይፈፅማል፤ የነበረበትን ዳስ እና ለአስክሬን የተሰራውን ቤት በማፍረስ ሁሉም ራሱን ለስራ ያዘጋጃል፡፡ ይህ ስርዓት በእኛ ማህበረሰብ ዘንድ እንደ ቀብሩ ቀን ሁሉ ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጠው በመሆኑ በተለያየ ምክንያት በቀብሩ ዕለት ያልተገኘ ሰው በዚህ ዕለት ደርሶ ሀዘኑን በመግለፁ በቀብሩ ዕለት ባለመድረሱ ምክንያት ተፈጥሮ የነበረው ቅሬታ ይወገድለታል፡፡
አራተኛው ቀን የተመረጠውም እንደዛሬው መንገድ በየአካባቢው ከመስፋፋቱ በፊት የእኛ ህዝብ ሰፍሮ የሚገኝበት አካባቢ ጥቅጥቅ ያለ ደን የሚበዛበት እና ኮረብታማ በመሆኑ ሁሉም ለቀስተኛ በቀብሩ ዕለት ከያለበት ተሰባስቦ መገኘት ባይቻለው በዚህ ቀን ደርሶ ሳይመቸው እንጂ ሆን ብሎ አለመሆኑ ከግምት ውስጥ እንዲገባለት የሚያደርግበትን እድል ለመፍጠር እና ሀዘኑ ሞት ከተፈጠረ በኋላ ከ1 እስከ 3 ወር ድረስ ሊቆይ የሚችል በመሆኑ ቀብሩ ከተፈፀመ ከአራተኛው ቀን በኋላ ሁሉም ወደቀድሞ ስራው መመለስ ይኖርበታል ብለው አባቶች በደነገጉት ደንብ መሰረት ነው፡፡
በአራተኛው ቀን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በሟች መቃብር ላይ ተገናኝተው ዘመድ አዝማዱ አልቅሶ ከመለያየቱ በፊት በመካነ መቃብሩ የነበራቸውን ቆይታ የሚፈፅሙት በመቃብሩ ላይ አስቀድመው ያዘጋጁትን የተለያዩ ዛፎች ችግኝ በመትከል እና አካባቢውን በማፅዳት ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *