




ቢሮው በሚዛን አማን ከተማ ሲያካሂድ የቆዬውን የ6 ወራት አፈፃፀምና የቀጣይ አቅጣጫዎች እንዲሁም ለተለያዩ የፋይናንስ ህግ ማዕቀፎች ዝግጅት ግብዓት ማሰባሰብ ላይ ያተኮረ ጉባዔ አጠናቋል።
ጉባዔው በቆይታው የ2016 በጀት ዓመት የ6 ወራት የአፈፃፀም ሪፓርት በስፋት የተወያየበት ሲሆን በሪፖርቱ በተለይም ሲንከባለል የመጣ የግብዓትና የጡረታ ዕዳ ለማስመለስ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ቢሆኑም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመላክቷል።
የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ እንደገለፁት ዕዳን ማሳደር በክልሉ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ በመሆኑ የጉባዔው ተሳታፊዎችና በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው ክፍሎች በቁርጠኝነት ወደተግባር በመግባት ከችግሩ መላቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢንስፔክሽን መዋቅሮችን የማጠናከር ስራ እና የኦዲት ግኝቶችን ተከታትሎ ሀብት በማስመለስ ረገድ ለነገ የማይባል ተግባር እንደሚጠበቅ በጉባዔው ተነስቷል።
በተጨማሪ በመንግስት በጀት ላይ ከተንጠለጠለ ልማዳዊ አሰራር በመላቀቅ የገቢ አሰባሰብ አቅማችንን በማዘመንና በማሳደግ እየተስተዋለ ያለውን የጥሬ ገንዘብ ዕጥረት መቅረፍ እንደሚገባ ኃላፊዋ ገልፀዋል።
በመድረኩ በርካታ የፋይናንስ የህግ ማዕቀፎች የአፈፃፀም ደንብና መመሪያዎች በቢሮው አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች ለውይይት ቀርበው ከተሳታፊዎች ተጨማሪ ግብዓቶችን ማሰባሰብ ተችሏል።
በጉባዔው ማጠቃለያ የፋይናንስ ህግ ማዕቀፎችን በጥብቅ ዲሲፒሊን በመፈፀምና በማስፈፀም ውስን የሆነውን የመንግስትና የህዝብ ሀብት ለታለመለት ዓላማ በማዋል “ከዕዳ ወደምንዳ የምንሻገር እንጂ ዕዳን የምናሻግር አመራሮች ልንሆን አይገባም” ሲሉ የቢሮ ኃላፊዋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ጉባዔ የክልል፥ የዞን፥ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ኃላፊዎች እንዲሁም የክልሉ ቢሮ ማኔጅመንት አባላት ተሳትፈዋል።
በእንዳለማው ጌታ
