የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ የ15 ዓመት የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ተገብቷል:-አቶ ኢብራሂም ተማም

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ የ2016 ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነዉ።

ጊዜውን የዋጀ ፍትሐዊነቱንና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር መሆኑም ተገልጿል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ የጤና ተደራሽነትን ፣ጥራትንና ፍትሃዊነትን በሁሉም ደረጃ በማረጋገጥ የእናቶችንና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ትኩረት በማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመድረኩ ባስተላለፉት የጤና አገልግሎት ፍትሐዊነት እና ጥራት ከማረጋገጥ አንጻር ብዙ ስራዎችን መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

የወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በህብረተሰቡ ላይ የከፋ ችግር ከማስከተሉ በፊት ርብርብ በማድረግ ሁላችንም ልንሰራ ይገባል ስሉ እክለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ የ15 ዓመት የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ የተቀዛቀዘው የጤና ኤክስቴንሽን ለማቀጣጠል ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል።

የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ፍላጎትና ተጠቃሚነትን መሠረት በማድረግ በሰለጠነ የጤና ባለሙያ የሚሰጠው የወሊድ አገልግሎት ፣በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር እንዲሁም ለእናቶችና ለህጻናት የሚደረጉ እንክብካቤ ፕሮግራሞች መሻሻሎች ታይተዋል ብለዋል።

ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚታመሙና የሚሞቱ የእናቶችንና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መሰራታቸዉን አቶ ኢብራሂም ገልጸዋል።

በጤና ተቋማት የሚሰጠው የእናቶች የወሊድ አገልግሎት ጥራት ትኩረት የሚሻ ተግባር እንደሆነም አብራርተዋል ።

በክልሉ 85 በመቶ ለሚሆኑ እናቶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት መስጠት ተችሏል ሲሉም አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል ።

እየተሰጠ ያለው የክትባት ስራዎች ጥሩ ቢሆኑም ከጥራት ጋር በተያያዘ ያሉ ስራዎች አሁንም ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ኃላፊዉ ጠቅሰዋል ።

መቀንጨርን ለመከላከል ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ከሆኑ ህጻናት 65 ከመቶ የሆኑ ህጻናት የስርዓተ ምግብ ልየታ መደረጉን ጠቅሰዋል።

የሃይጂንና ሳኒቴሽን ተግባራት ዛሬም የሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ትኩረት የሚሻ መሆኑን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው የተሻሻለ መጸዳጃ ቤት ግንባታ በተቋማትና በግለሰብ ደረጃ ግንባር ቀደም አጀንጃ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን ስራዎች የተቀዛቀዘ በመሆኑ በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭት ሁሉም አካባቢዎች ተከስቷል ።

የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን በመለየት የማዳፈንና የማፋሰስ ስራዎች መሰራታቸውንም አቶ ኢብራሂም ገልጸዋል።

እስካሁን ከ 1.2 ሚሊየን በላይ የአልጋ አጎበር መሰራጨቱንና የወባ በሽታ ጫና ባለባቸው ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የቤት ለቤት የአልጋ አጎበር ስርጭት ሽፋን 92.6 ከመቶ መድረሱን አስገንዝበዋል ።

የማህጸን በር ጫፍ ክትባት አገልገሎት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ በመሆኑ ይህም በልዩ ትኩረት የሚሰራ ተግባር መሆኑን አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል ።

በስራ ዘመን ቆይታቸው በጡረታ ለተሸኙ የጤና ባለሙያዎች ቢሮዉ ሽኝት አድርጎላቸዋል።

በበጀት ዓመቱ ዉጤታማ ተግባራት ለፈጸሙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እና የወረዳ ጤና ጽ/ቤቶች የእውቅና ሰርተፊኬትና ሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የቢሮው የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣የዞንና የወረዳ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ታርጫ ከተማ እየተገመገመ ነው።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *