




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከስር መዋቅሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአስር ዓመት መሪ ዕቅድ ክለሳ፣ በ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ የምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በምክክር መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ የዘመናት የህዝብ ቁጭትና የትግል ውጤት የሆነው ዳግም አድዋ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በመመረቁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
አክለውውም ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ በፍርድ ቤቱ የተሰሩ ስራዎች፤ ከታችኛው መዋቅር ጋር ያለው ግንኙነት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የተጠያቂነት አሠራርን ከመዘርጋት እና ሌሎች አፈጻጸሞች ከዓመት ወደ ዓመት እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም በበጀት ዓመቱ በተገኙ በጥንካሬና በድክመት በሚነሱ ጉዳዮች እንዲሁም ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ተሳታፊዎቹ በጥልቀት በመወያየት በቀጣይ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በቅንጅት እንዲሰሩ ዋና አፈ ጉባኤው አሳስበዋል።
በጉባኤው ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማሪያም ፍ/ቤቶች የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ጥቅሞችን ለማስከበር ተቋማዊ እና ግለሰባዊ የዳኝነት ነጻነትን በማስጠበቅ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ተጋማችና ተደራሽ የሆነ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት የህግ በላይነትን በማስፈን የህዝብ አሜኔታ ለማትረፍ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል ።
በ2017 ዓ/ም በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ካለፈው በጀት ዓመት የተሻገሩ 1949 የወንጀልና የፍትሐብሔር መዝገቦች እንዲሁም አዲስ ከቀረበው 59,983 በድምሩ 61,932 ከቀረቡት መዝገቦች ውስጥ 60,441 መዝቦች ውሳኔ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።
ክልላዊ አማካይ በጥረት ተደራሽ ግቦች አፈጻጸም የመወሰን አፈጻጸም 97.58% ፣የማጥራት አቅም አፈጻጸም 102%፣ የፋይሎች የመጨናነቅ ሁኔታ አፈጻጸም 1.02፣ እና በሁለት ወር የመወሰን አቅም አፈጻጸም 90.66% መድረሱን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል።
የዳኛ የመዝገብ ጥምርታ 1ለ99 ፣ የሚሻሩ ውሳኔዎችን የመቀነስ ስራ አፈጻጸም 83.22% ማድረስ መቻሉንም አክለው አንስተዋል።
በመሆኑም በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ በርካታ የተሻሉ ውጤቶች የውጪና የውስጥ ተግዳሮቶችን በመጋፈጥ መሆኑን በማስታወስ የፍርድ ቤቶች ስራ በዳኝነት አካሉ ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ በየደረጃ የሚገኙ የባለድርሻ አካላት ትብብር፣ ድጋፍና ቅንጅት እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ተናግረዋል ።
የክልሉ ፍርድ ቤቶች የ2017 ዓ/ም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የጠቅላይ ፍ/ቤት የልማት ዕቅድ ዳይረክቶሬት ዳይሬክተሩ በሆኑት አቶ ጥላሁን ወ/ማሪያም እና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የ2017 ዓ/ም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በዞን አቅራቢዎች ለተሳታፊዎቹ እየቀረበ ይገኛል።
በጌታሁን ግርማ
