
የ2018 ዓ.ም የካፈቾ ዘመን መለወጫ ማሽቃሮ በዓልን አስመልክቶ የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻ ከበደ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዓሉ ለዓመታት መከበር ካቆመ በኃላ በ1986 ዓ.ም የባህል እና ቋንቋ ስምፖዚዬም መካሄዱን ተከትሎ በ1998 ዓ.ም በድጋሜ መከበር መጀመሩን ያወሱት ዋና አስተዳዳሪው ዘንድሮ በልዩ ድምቀት ድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በዓሉ ህዝባዊ መሠረት ያለው በመሆኑ ላለፉት 20 ዓመታት ወቅቱ በደረሰ ጊዜ ከቀበሌ ጀምሮ ሲከበር የቆየ መሆኑንጨ የተናገሩት አቶ እንዳሻው በአሁኑ ወቅት በወረዳ ደረጃ በድምቀት እየተከበረ መሆኑን አንስተው በመስከረም 12 በካፋ መናገሻ ቦንጋ ከተማ ፓናል ውይይት ተደርጎ በመስከረም 13 በቦንግ ሻንበቶ ማጠቃለያውን ያገኛል ብለዋል።
በዓሉ ከህዝባዊ መሠረትነት ተሻግረው በዓለም ደረጃ ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት ትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም(UNESCO) ላይ እንዲመዘገብ ስራዎች ተጀምሯል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ለዚህም ከክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ፣ ከፌደራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን እና ከባህልና ስፖርት ሚንስትር ጋር እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
የዘንድሮ ማሽቃሮ በሁለት ትላልቅ ስኬቶች የታጀበ ልዩ በዓል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ሀገራችን ቀና ያለችበት የህዳሴ ግድብ መመረቁና ከ128 ዓመታት በፊት የካፋ ነገስታት ዘውድና ዙፋን ወደ ስውዘርላንድ ዙሪክ ተወስዶ የነበረው በኋላም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሶ ቆይቶ አሁን በዓሉን ለማክበርና ለማድመቅ ቦንጋ መምጣቱ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በተለያዩ አብይና ንዑሳን ኮሚቴ ተዋቀረው ሰፊ ቅድመ ዝግጅት መሠራቱን የገለፁት ዋና አስዳደሪው በዝህም ከተለያዩ ተቋማት፣ ኤምባሲዎች እና የሀገራችን ክፍሎች ለሚመጡ እንግዶች የካፋ ብሔረሰብ በሚታወቅበት እንግዳ አቀባበል ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል ።
በመጨረሻም አቶ እንዳሻው መላው የካፋ ህዝብ እና ወዳጆች ይህን ታላቅ በዓል እንዲታደሙ ጥሪያቸውን አቅርበው በድጋሜ እንኳን ለታላቁ ህዝብ ማሽቃሮ በሠላም አደረሳችሁ ብለዋል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
