ቢሮው ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የሚያደርገውን የስነ ልቦናና የቁሳቁስ ድጋፍ አጠናክሬ እቀጥላለሁ አለ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ በክልሉ በተለያዩ ሁኔታዎች ፆታዊ ጥቃት ሰለባ ለሚሆኑ ሴቶች አገለግሎት የሚውል ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፊ አደረገ።

ድጋፉ በክልሉ በሚገኙ በአራቱ ጠቅላላ ሆስፒታሎች የህክምናና የስነ ልቦና እርዳታ ለሚያገኙ ተጠቂ ሴቶች በነፃ የሚደረግ እንደሆነም ተገልጿል።

በክልሉ ከሚገኙ ከአራት ጠቅላላ ሆስፒታሎች መካከል አንዱ ለሆነው ለታርጫ ጠቅላላ ሆስፕታል የቁሳቁስ ድጋፎችን ያስረከቡ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም የተደረጉ ድጋፎች ለተባለለት አላማ ብቻ እንዲውሉ አሳስበዋል።

እነዚህ በነፃ የሚሰጡ ድጋፎች በተገቢው አገለግሎት ላይ መዋላቸው ኦዲት እንደሚደረጉም ሀላፊው አስረድተዋል።

በቢሮው የስርዓተ ፆታ ተወካይ ወ/ሮ ዳግም ከበደ በበኩላቸው ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት መከላከል ላይ ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ቢሆንም የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ፆታዊ ጥቃት በቤተሰብ፣ በቅርብ ጓደኛ በማስፈራራት፣ በማታለልና በጉልበትም ጭምር የሚፈፀሙና እጅግ ፀያፍ ተግባር በመሆኑ በጋራ ልንከላከል እንደሚገባም ተናግረዋል።

ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው እህቶች የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ በሚዛን ቲችንግ ሆስፕታል ተቋቁሞ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑም ተገልጿል ።

የአንድ ማዕከሉን አገለግሎት በክልሉ በሌሎች ሆስፒታሎች ለማስፋፋት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛልም ተብሏል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *