




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ግብርና ቢሮ የ2017 ዓ.ም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና መደበኛ መስኖ ሥራዎች አፈጻጸም እንዲሁም የ2018 ዕቅድ ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በወቅቱ እንደገለጹት፤እንደሀገር በምግብ ራስን መቻል፣ተተኪ ምርት ማምረት እና የምግብ ልዑላዊነት ለማረጋገጥ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።
በሀገራችን ብሎም በክልላችን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በከፍተኛ ሁኔታ እየተለመደና ከውጪ የሚገባውን በመተካት የምግብ ፍላጎት እያሟላ እንደሚገኝም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።
በክልሉ ዓመታዊ የስንዴ ሽፋን ከ30-50 ሺህ ሄክታር መድረሱንና ስንዴ በመኸር ላይ ከሚመረተው በበለጠ በበጋ መስኖ እየተመረተ ይገኛል ያሉት አቶ ማስረሻ ዘንድሮ 10 ሺህ ሄክታር ማሳ በበጋ መስኖ ለማልማት መታቀዱንም ጠቁመዋል።
በክልሉ 18 ሺህ ሄክታር ማሳ ማልማት የሚችል 93 የመስኖ አውታር ፕሮጀክቶች እንዳሉትም አንስተው የተፈጥሮ እርጥበትንና የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ምርቱን በስፋት ማምረት ይጠበቅብናል ብለዋል አቶ ማስረሻ በላቸው።
በክልሉ በዘንድሮ ዓመት 62 ሺህ 276 ሄክታር ማሳ በበጋ ስንዴ ልማትና በ1ኛ ዙር መስኖ (በስራ ሥርና በአትክልት) እንደሚለማ የተናገሩት አቶ ማስረሻ ከዚህም 19 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃልም ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የተያዘውን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ እንዲሳካ ከወትሮ በተለዬ በቁርጠኝነት እና በላቀ ቁርጠኝነት ማከናወን ይጠበቃልም ብለዋል።
በመድረኩ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና መደበኛ መስኖ ሥራዎች አፈጻጸም እንዲሁም የ2018 ዕቅድ ላይ የተዘጋጁ ሰነዶች እየቀረቡ ይገኛሉ።
በፍቅር ከበደ
