በክልሉ ሠላምን በማጽናት ልማትና እንቨስትመንትን ማስፋፋት እንደሚገባ ተጠቆመ።

Spread the love

“ሠላምን በማጽናት በልማት ማንሰራራት” በሚል መርህ ቃል በኢፌዴሪ የሠላም ሚኒስቴር፤ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሠላምና ፀጥታ መዋቅር የተዘጋጀው ስልጠና በሚዛን አማን ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።

በስልጠናው መድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ፣ ምክትል የቢሮ ሀላፊ አቶ ሀብታሙ አለሙ፥ በክልሉ አለመግባባትና ግጭቶችን ማኅበረሰብን ባሳተፈ ውይይት መፍታት በመቻሉ አወንታዊ ሠላም መስፈኑን ተናግረዋል።

የተገኘውን ሠላም ዘላቂነት በማረጋገጥ ክልሉን ለልማትና ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ በንግግራቸው።

የፀጥታ ችግር በሚስተዋልባቸው የክልሉ አከባቢዎች ላይ ተከታታይነት ያለው ማኅበረሰብን ያሳተፈ ውይይት በማድረግ እንዲሁም የፀጥታ መዋቅር በማቀናጀት ሠላም ማስፈን ተችሏል ያሉት አቶ ሀብታሙ የተገኘውን ሠላም በዘላቂነት ማጽናት ይገባል ብለዋል።

በየደረጃው ያለው የፀጥታ መዋቅር አመራሮች ለሠላም መስፈንና ለዘላቂ ሠላም ግንባታ ህዝቡን የሠላም ባለቤት በማድረግ መንቀሳቀስ እንደሚገባም ነው አቶ ሀብታሙ አክለው የገለጹት።

ስልጠናው ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ግጭቶችን በመፍታትና ዘላቂ ሰላምን በመገንባት ረገድ የተሟላ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መኾኑን ነው በኢፌዴሪ የሠላም ሚኒስቴር፣ የሥራ አመራር ዋና ስራ-አስጻሚ አቶ መብራቱ ካሣ የገለጹት።

እንደ አቶ መብራቱ ገለጻ፥ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በዘላቂ ሠላም ግንባታ፣ በማኅበረሰብ አቀፍ የግጭት አፈታት እና የፀጥታ መዋቅር ቅንጅትና የመፈጸም አቅም ዙሪያ በየደረጃው ስልጠናና ግንዛቤ እየፈጠረ መጥቷል።

ሠላምን ማጽናት እጅግ ጥንቃቄና ቁርጠኝነት የሚፈልግ ተግባር መኾኑን የገለጹት አቶ መብራቱ በዚህ ረገድ ስልጠናው ለቀጣይ ተልዕኮ የሚያዘጋጅ እንደኾነ አስረድተዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፌዴራሊዝምና መንግስታት ግኑኝነት መሪ ስራ-አስፈጻሚ አቶ ግርማ ቸሩ የመወያያ ሰነድ እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ ዝርዝር ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በመድረኩ የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽን ሰብስቤ ሸዎኖን ጨምሮ ምክትል ኮሚሽነሮች እና የክልሉ የፀጥታ መዋቅር አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *