




ለ18ኛ ጊዜ ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመይ ብስራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነትና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ በሚል መሪ ቃል በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተከብሯል ።
በክልሉ ታርጫ ከተማ የተገኙ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ወንድሙ ኩርታ እንደገለፁት ኢትዮጵያ ነፃነቷን ከማስከበር ባለፈ ለሌሎች ነፃነታቸውን ለተነጠቁ የአፍሪካ አገራት ነፃነት ፈንጣቂ አገር በመሆን የድርሻዋን ተወጥታለች።
ከዚህ የተነሣ በኢትዮጵያ በጀብዱነትና በአገራዊ አርበኝነት ሰንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያን የሚወክል ሲሆን የሰንደቅ ዓላማ ቀን የማንነት መገለጫ ታላቅ ክብረ በዓል መሆኑንም ተናግረዋል።
ስለሆነም ዜጎች የማንነት መገለጫ አርማ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር በመስጠት የጋራ እሴቶችን በመገንባትና መግባባትን በሚፈጥር ሁኔታ ማክበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን ወቅታዊና አገራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ ሁኔታ ማክበር ከተጀመረ 17 ዓመታት አስቆጥሯል።
የዘንድሮውን በዓል ስናከብር በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ ለመሆን ቃላቸውን የሚያድሱበት ዕለት ሲሆን ዳግም አድዋ የሆኑ የዓባይ ግድብ በተመረቀበትና የተፈጥሮ ጋዝ ምርት በተጀመረበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋልም ብለዋል።
በዓሉ በፓናል ውይይትና በተለያዩ የፖሊስ ትርኢት የተከበረ ሲሆን የሰንደቅ ዓላማ በመስቀል ከፍ የማድረግ ኩነቶች ተፈጽመዋል።
በቦታውም አንድነትን ለማጠናከርና አገራዊ ተልዕኮን በትጋት ለመወጣት እንዲቻል ቃለመሃላም ተፈጽሟል።
በዕለቱ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ፣ የዳዉሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁና የዞኑ አፈ ጉባዔ አቶ ዳዊት ሚኖታን ጨምሮ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮችና አጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የፖሊስ አባላት ተሳትፈዋል።
