የቆላማ አከባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶችን ከመንግሥት መደበኛ ተግባራት ላይ ማስተሳሰር ይገባል፦ አቶ ማስረሻ በላቸው

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአርብቶአደርና ቆላማ አከባቢዎች ጉዳይ ቢሮ፥ ምዕራፍ ሁለት የቆላማ አከባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ የእስትሪንግ ኮሚቴ ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ የ2018 በጀት ዓመት ዝርዝር ዕቅድ በፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ደረጀ በቀለ ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ተግባራትን ከመንግሥት መደበኛ ተግባራት ላይ ማስተሳሰር እንደሚገባም ነው የእስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የገለጹት።

በፕሮጀክቱ የሚከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ከግጦሽ አስተዳደር ጋር የተቆራኘ መኾኑን የጠቆሙት አቶ ማስረሻ ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የተጀማመሩ ፕሮጀክቶችን በትኩረት በማጠናቀቅ የአርብቶና ከፊል አርብቶአደር ህይወት በዘላቂነት ማሻሻል እንደሚገባ የገለጹት አቶ ማስረሻ በፕሮጀክቱ ቀጠና ተጨባጭ መነሻ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የመንግሥት የልማት ክፍተቶችን እየሞላ ነው ያሉት የክልሉ የአርብቶአደርና ቆላማ አከባቢዎች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ መቱ አኩ የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዘላቂ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ፕሮጀክቶችን በማቀናጀት መምራት እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ መቱ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር መጠናከር አለበት ብለዋል።

የእስሪንግ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው፥ የሚከናወኑ የፕሮጀክቱ ተግባራትን ከመንግሥት ኢንሼቲቮች ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ በኾነ መልኩ መፈጸም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የእንስሳት ጤና አገልግሎቶችን እና የአንድ ጤና መርህዎች (One Health Approach) በማጠናከር በአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ከእንስሳት ወደ ሰው ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች የሚያስከትሉት ከፍተኛ ጉዳቶች መቀነስ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ለማስተዳደር የተረከቡ የመንግሥት ተቋማት የተጣለባቸው ሀላፊነት በአግባቡ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።

የእስትሪንግ ኮሚቴው ምዕራፍ ሁለት የቆላማ አከባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የ2018 በጀት በዝርዝር በመገምገም አጽድቋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *