የክልሉ መንግሥት ለአርቲስቶች የእውቅናና ሽልማት መርሃግብር አደረገ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትለው “የእንኳን ደስ ያላችሁ” ሙዚቃ በማዘጋጀት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የክልሉ አርቲስቶች እውቅናና ሽልማት አበርክተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ አርቲስቶች በኪነ ጥበብ ስራ ለሀገር ልማትና ለክልላዊ አንድነት በጎ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አርቲስቶቹ ቀድም ሲል “ዋሴ፣ዋሴ” በተሰኘው የሙዚቃ ስራ ላይ በመሳተፍ እንዲሁም በግድቡ ምረቃ ወቅት የምስጋና ሙዚቃ በማዘጋጀት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።

ከዚህም ባሻገር በየአካባቢው በባህል ልማት እንዲሁም ታሪክና ወጎችን በኪነጥበብ ስራዎቻቸው በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና እንደነበራቸውም ጨምረው ገልጸዋል።

በቀጣይ የክልሉ መንግሥት ተቀራርቦ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ አርቲስቶቹ ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

አርቲስቶቹ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ላደረገው እውቅናና ሽልማት አመስግነው በቀጣይ ተቀራርበው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት የሰጠው እውቅናና ሽልማት ለተጨማሪ ስራዎች የሚያነሳሳ እንደሆነም አርቲስቶቹ ተናግረዋል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ የክልሉ አስተባባሪ አካላት ተገኝተዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *