የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክርቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የአስፈጻሚ አካላት የ6 ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክርቤት እያቀረቡ ነው ።

ባቀረቡት ሪፖርታቸው ወቅታዊ ክልላዊ ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከክልል ማዕከል ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ 2 ሺህ 221 አመራሮችን የመገምገምና የማጥራት ስራ በልዩ ሁኔታ መከናወኑን ተናግረዋል ፡፡

በዚህም በማጥራት ሂደት ውስጥ የተለያዩ ብልሽት የተስተዋለባቸው 61 አመራሮች ከኃላፊነት እንዲነሱ፣ 36 አመራሮች የቦታ ሽግሽግ እንዲያደርጉ 442 አመራሮች ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ተደርጓል ብለዋል ።

ከሙስና፣ ሌብነት እና ብልሹ አሠራርን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር የጸረሙስና ኮሚቴ በማደራጀት ጥቆማዎችን መውሰድና መረጃዎችን የመተንተን ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን በኦዲት ሪፖርት መሠረት የተመዘበረውን የመንግሥትና የሕዝብ ሃብት በህጋዊ መንገድ የማስመለስ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራና የኦዲት ግኝትን መሠረት በማድረግ ብር 19,192,685 ፣ 1,890.5ሄ/ር የገጠር መሬት፣ 26,705.51 ካሬ ሜትር የከተማ እንዲሁም ሁለት የከተማ መኖሪያ ቤቶች እንዳይሸጡ፣ እንዳይለወጡና ለሶስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ የማሳገድ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡

በወንጀሉ የተጠረጠሩ ግለስቦችም ጉዳያቸው በህግ አግባብ እየታየ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ከግብርና ስራዎች አኳያ በ2015/16 የምርት ዘመን ከ5 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ብለዋል።

በ2015/16 የምርት ዘመን በመኸር ወቅት በዋናዋና አዝዕርት ሰብሎች 327 ሺህ 908 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል ።

በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 282 ሺህ 394 ሄክታር ማሳ የለማ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 82 በመቶ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል ።

ያልተሰበሰው ምርት በማሳ በመድረስ ላይ የሚገኝ ሲሆን የማሰባሰቡ ስራ በቀሪ ጊዜያት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 7 ሺህ 127 ሄ/ር መሬት በማልማት ከ285 ሺህ በላይ ኩ/ል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል ።

የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራዎችን ለመተግበርም በክልሉ በ2016 ዓ/ም 1 ሺህ 88 ሄክታር ንዑስ ተፋሰሶች የመለየትና ጥናትና ዲዛይን ስራዎችን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

በቡና ምርት ሂደት በግማሽ ዓመቱ ከ22 ሺህ በላይ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንደቀረበም በሪፖርታቸው አብራርተዋል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *