


ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ለክልሉ ምክርቤት ባቀረቡት ሪፖርት ባለፉት ስድስት ወራት ለ33 አዳዲስ ፕሮጀክቶች ፍቃድ መስጠት እንደተቻለ አብራርተዋል ።
የክልሉን የኢንቨስትመንት ዕድሎችንና ምቹ ሁኔታዎችን በማስተዋወቅ አቅም ያላቸውን ነባርና አዲስ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችን በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በትኩረት ተሰርቷል ሲሉም ተናግረዋል ።
በዚህ መሰረት 44 በግብርና ፤ 36 በኢንዱስትሪ አዲስ ኢንቨስትመንት ፍቃድ ለመስጠት ታቅዶ በግብርና 26፤ በኢንዱስትሪ ለ7 ፕሮጀክቶች አዲስ ፈቃድ መስጠት ተችሏል ሲሉም ተናግረዋል ፡፡
ከኢንቨስትመንት ካፒታል ምዝገባ አንፃር በግብርና ፕሮጅክቶች 2,173,000,000 ለማስመዘገብ ታቅዶ ብር 4,489,000,000 ፣ በኢንዱስትሪ ፕሮጅክቶች 427,500,000 ብር ለማስመዘገብ ታቅዶ ብር 340,000,000 መመዝገብ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ለዜጎች በተለያዩ የስራ ዘርፎች በቋሚ ለ33ሺህ 390 የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ በከተማ 6341፣ በገጠር 16 ሺህ 921 እንዲሁም በተቋማት 3 ሺህ 186 በድምሩ 26 ሺህ 498 ስራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ አብራርተዋል ፡፡
በክልሉ መንግስት የታቀዱ የመሠረተ ልማት፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ ልማት እና የመልካም አስተዳደር ግቦችን ለማሳካት በግማሽ አመቱ 3 ቢሊዮን 106 ሚሊየን 518 ሺህ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ብር 2 ቢሊዮን 721 ሚሊዮን 466 ሺህ 156 ብር ከ45 ተሰብስቧል ብለዋል፡፡
ይህም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 717 ሚሊዮን 882 ሺህ 710.48 ብልጫ እንዳለው በሪፖርታቸው አብራርተዋል ፡፡
የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ እንዲጠናከር መላው የክልሉ ህዝብ የበኩልን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
በታጠቅ አበበ
