




የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸዉ እንዳስታወቁት፤የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የግብርና ፓኬጆችን በተገቢዉ ሁኔታ ተግበራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምርጥ ዘርን መጠቀም ከፍተኛ ዉጤትን የሚያስገኝ በመሆኑ የምርጥ ዘር አቅርቦትን ለማሳደግ እንዲቻል የምርጥ ዘር ድርጅትን በማቋቋምና በርካታ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ዉጤታማ ተግባራትን እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህን በፊት ምንም ዓይነት ምርጥ ዘር ከማይመረትበት ክልል አሁን በአንድ ወቅት ብቻ ከ2ሺህ7መቶ እስከ 3ሺህ 2መቶ ሄክታር በክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት፣በክልሉ በዚህ ዘርፍ በተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር በአጋርነት ማምረት የተጀመረበት ሁኔታ መኖሩን አቶ ማስረሻ ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮዉ መኸር ወቅት ሶስት ዋና ዋና የሰብል ዓይነቶችን በማልምት ምርት እየተሰበሰብ እንደሚገኝ ጠቁመዉ ከዚህ መነሻ በበልግ አዝመራ ዘጠኝ የሰብል ዓይነቶችን ለማልማት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትየጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ብርሃኑ ብላቴ በበኩላቸዉ፤በ2017/20118 የመሄር ምርት ዘመን ከ90 ሄክታር መሬት በላይ የተለያዩ ሰብል የዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
እስካሁንም በመኄር አዝመራ በ90 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ፣የበሎቄና ሩዝ ሰብሎች የዘር ብዜት ሥራው መከናወኑን ገልጸዉ ከዚህም ከ3ሺህ በላይ ኩንታል ምርት እንደሚገኘም አስረድተዋል።
ድርጅቱ ለክልሉ አርሶ አደርና በግብርናው ለተሰማሩ የግል ባለሀብቶች ምርጥ ዘር ለማቅረብ የሚስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝና በክልሉ የምርጥ ዘር ፍላጎት ለማሟላት የተጀመረው ስራ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ ነዉ ብለዋል፡፡
የዘር ብዜት ስራው እየተናወነ ያለው በአርሶ አደር ማሳ፣በማህበራት እንዲሁም ከግለሰቦች ጋር ዉል በማዋዋል እና ድጋፍ በማድረግ መሆኑን አመልክተዉ በዕቅድ የተያዘውን የዘር ብዜት ሥራ ለማሳካት ስራው በተቀናጀ አግባብ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በድርጅቱ የዘር ጥራት ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ደረጀ በላቸዉ፤በኮንታ ዞን ኮንታ ኮይሻ ወረዳ በሀመካ የእርሻ ጣቢያ በ50 ሄክትር መሬት ላይ እየለማ ካለዉ የሩዝ ምርጥ ዘር ብዜት ስራ ከ2ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብም ጠቁመዋል፡፡
የክልሉን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የምርጥ ዘር አንዱ ማነቆ በመሆኑ በግብዓት አቅርቦት ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ተቋሙ አግሮ-ኢኮሎጂን ታሳቢ ያደረገ ምርጥ ዘር ብዜት ስራ እያከናወነ መሆኑን አክለዋል።
በካፋ ዞን አዲዮ ወረዳ የቦቃ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አላሎ አበበ በቀበሌዉ 20.25 ሄክታር የስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት ስራዉ በ19 አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም መልማቱን አስረድተዋል።
ለስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት ማሳ ዝግጅት፤የግብዓት አቅርቦት ስራዎች እና በሌሎች ስራዎች የተጠናከረ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዉ ከዚህም 1ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ለማቅረብ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የቀበሌዉ አርሶ አደር አስራት ክፍሌ በማዳበሪያ እና በምርጥ ዘር አጠቃቀም የዳበረ ልምድ እንዳላቸዉ አዉስተዉ በክላስተር ከለማዉ ስንዴ ጥሩ ዉጤት ለማግኘት የእንክብካቤ ስራዉን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ከክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት ጋር ውል ፈጽመው በ10 ሄክታር መሬት ላይ የበሎቄ ዘር እያባዙ እንደሚገኙና ከሚያባዙት የበሎቄ ዘር ጥራቱን የጠበቀ ዘር ለመሰብሰብ ተግተው እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት በዳዉሮ ዞን ተርጫ ከተማ ቀበሌ 01 አርሶ አደር ተሾመ ሃይሌ ናቸዉ።
በዳዉሮ ዞን የታርጫ ዙሪያ ወረዳ ገሳባሌ ቀበሌ አርሶ አደር ታዬ ኦዳሞ በ3 ሄክታር ማሳ ላይ የበሎቄ ዘር ብዜት በማህበር እያለሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በካሳሁን አሰፋ
