
በሸካ ዞን በቅርቡ በተደረገው ጥብቅ ግምገማ ላይ ተመስርቶ በተወሰደው እርምጃ ከዞን እስከታችኛዉ መዋቅር 108 አመራሮችን ከኃላፊነት የማንሳት ፣የማሸጋሸግና በአዲስ መልክ ወደ ኃላፊነት የማምጣት ስራ ተሠርቷል ሲሉ የሸካ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ አለሙ ገልፀዋል።
በቀጣይ ጊዜያት የፓርቲና የመንግስት ተልዕኮን በተገቢው መፈፀምና ማስፈፀም የሚችል የአመራር ስምሪት ተሰጥቷል ሲሉም አክለዋል አቶ አለማየሁ።
አቶ አለማየሁ እንደገለጹት ይህ እርምጃ የተወሰደው ፓርቲው ያለፈውን ዓመት አፈጻጸም በጥልቀት ከመዘነ በኋላ መጪውን ተልዕኮ በብቃትና በስነ ምግባር ሊያስፈጽም የሚችል ጠንካራ አመራር ለመፍጠር ነው ብለዋል።
አቶ አለማየሁ አያይዘውም 34 አመራሮች ከኃላፊነት የተነሱ፣35 አመራሮች የተሸጋሸጉ ሲሆን 39 ደግሞ አዲስ ወደ አመራርነት የተቀላቀሉ መሆናቸውን ጠቁመው በአጠቃላይ 108 አመራሮችን ከኃላፊነት የማንሳት፣ የማሸጋሸግና አዲስ ምደባ የመስጠት ተግባር ተከናውኗል ሲሉ ገልፀዋል።
አቶ አለማየሁ አክለውም ጠንካራ ፓርቲ የመመስረት ግባችንን ለማሳካት በተግባር ውጤታማ የሆነና መልካም ስነምግባር የተላበሰ አመራር ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የተቋም ግንባታ ስራውን በቁርጠኝነት የሚመራ በዋናነትም ፓርቲያችን ሰው ተኮር በመሆኑ በየተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎት ለሰው ልጅ ያለንን ክብር የሚያሳይና ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሁም ከኪራይ የፀዳ እንዲሆን በቁርጠኝነት መስራት በአዲስመልክ የተመደበ አመራር የሚጠበቅበት ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል አቶ አለማየሁ።
በየመዋቅሩ ምደባ የተሰጣቸው አመራሮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተገቢው እንዲወጡ አሳስበዋል አቶ አለማየሁ ሲል የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
