በአንደኛ ዙር የበጋ መስኖ በስንዴና ሆልቲካልቸር ከ10 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች መንግስት ግብርና ቢሮ በምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በጀት ድጋፍ የተዘጋጀ የበጋ መስኖ ስንዴ እና መደበኛ መስኖ አመራረት ፓኬጅ አሰልጣኞች ሥልጠና በሚዛን አማን እየተሰጠ ነው።

በክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻና ሆልቲካልቸር ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ እንደገለጹት ግብርና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሆኖ እንደቀጠለ ተናግረዋል ።

የግብርና ምርትና ምርታማነት ለውጥ አምጥቶ ሀገርን ከመመገብ አልፎ ለሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ግብዓት መሆን እንዲችል የዘርፉን ባለሙያዎች ብቃትና ክህሎትን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

አክለውም የበጋ መስኖ የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የምግብ ዋስትናችን እንዲረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

በአንደኛ ዙር መስኖ ስራ ከ63 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በዘር ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሸናፊ ከዚህ ውስጥ 10 ሺህ ሄክታር በላይ በበጋ መስኖ ስንዴ እንዲሁም ቀሪው በሆልቲካልቸር እንደሚሸፈን ገልጸዋል።

ይህን ለማሳካት የሚችል የአሰልጣኞች ስልጠና በሶስት ክላስተር ከ250 በላይ ለሆኑ ባለሙያዎች እየተሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል ።

በአንደኛ ዙር የበጋ መስኖ በስንዴና ሆልቲካልቸር ከ10 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል አሰፋ በበኩላቸው ሀገራችን ስንዴን ከውጭ ከማስገባት አልፎ ራሷን በምግብ ዋስትና የመቻል ሂደት ለዘርፉ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

አክለውም የአሰልጣኞች ስልጠናው በዘርፉ የሚስተዋለውን ጉድለቶች በመቅረፍ አርሶ አደሩ ተገቢውን ቴክኖሎጂዎች እንዲጠቀምና ምርትና ምርታማ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።

አቶ ሳሙኤል አያይዘውም በተለያ ፕሮግራሞች ተገዝተው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የግብርና መሣሪያዎችን ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባልም ብለዋል።

በመደበኛ መስኖ በሆልቲካልቸር ላይ ምርታማነትን ለማረጋገጥ ከምንም ጊዜ በላይ ትኩረት መስጠት እንደሚባም አቶ ሳሙኤል ማሳሰባቸዉን የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

በስልጠናው ዘርፉ የሚመለከታቸው የዞንና የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *