የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን የዋና የፕሮጀክቶች አፈጻጸምን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ ገምግሟል

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንገዶች ባለስልጣን ዋና መስሪያ ቤት እየተሰሩ ያሉ የመንገድ ጥገናና ድልድይ ፕሮጀክቶች ያሉበት ደረጃ ገምግመው ቀጣይ በሚጠናቀቁበት ጉዳዮች ላይ ከአማካሪዎች፣ ተቋራጮችና ባለድርሻ አካላት ጋር መክረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት በግልፅ ጨረታ አሸንፎ ወደ ስራ የገቡት አራት የስራ ተቋራጮች እና ሁለት አማካሪ ድርጅቶች እየተሰሩ ያሉ የኮቾ፣ኡሜ እና መንሳ ድልድዮች እንዲሁም ዳካ-ሳይለም ሎት 2 መንገድ መልሶ ግንባታ አፈፃፀም ያለበት ሂደት ተገምግመዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጅዮ ሳፒ: በክልሉ የመሠረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት ቢሮውና ተጠሪ ተቋማት በቅንጅት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ጠቁመዋል።

አማካሪዎችና ተቋራጮች በገቡት ዉል መሰረት ሥራዉን ሰርተዉ ማስረከብ እንዳለባቸዉ ኃላፊዉ ገልጸዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለክልሉ ህዝብ የተቀናጀ ልማትን ለማረጋገጥ የተለያዩ መንገዶችንና ድልድዮችን በማጥናት ህዝቡን፣ ባለሀብቱንና ግብረሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበር አቅም የፈቀደውን ተግባራት እየፈጸመ እንዳለ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አብድዩ መኮንን ገልጸዋል።

ኢንጂነር አብድዩ አክለውም አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን በአየር መቀያየር ጫና መሆኑ ግልፅ ቢሆንም በያዝነው በጀት ዓመት ከቀድሞዎቹ ትምህርት በመውሰድ ከወዲሁ ዝግጅት ተደርገው ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ለባለድርሻ አካላት አስገንዝበዋል።

እንደ ሀገር የፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ስርዓት መቀየሩን ያነሱት የርዕሰ መስተዳደሩ መሠረተ ልማትና ኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪ አቶ ታምራት ቦጋለ: በክልላችንም በቀን 24 ሰዓት እና ሳምንቱን ሙሉ በመጠቀም በተፈለገው ጥራት ሰርቶ ማስረከብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በውይይቱ ወቅት አስተያየት የሰጡት ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የአብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያቶች ብዙ ብሆንም ዋነኝው ውል ከተገባ በኃላ የዝናብ ወቅትን ታሳቢ አድርገው በጊዜ ወደ ስራ ያለመግባት እንደሆነ አመላክተዋል።

በቀጣይም የጥራት ጉዳይን በማስቀደም የጠቅላይ ሚኒስሩን የፕሮጀክት ክትትል ተሞክሮ በማድረግ ሌት ተቀን ክትትል በማድረግ የክላሉ ኢኮኖሚ የሚያደናቅፍ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ የጋራ አቅጣጫ ተቀምጠውለት ውይይቱ ተጠናቋል።

በአሻግሬ ገብረወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *