



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የ2018 የአንደኛ ሩብ ዓመት የአፈጻጸም ግምገማ እና በቀጣይ አቅጣጫ ላይ የሴክተር ጉባኤ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ተቋሙ ባለፋት ጊዜያት በየደረጃው ያለው የፀጥታ መዋቅር በማቀናጀትና በመናበብ በሰራው ስራ ውጤታማ ስራ እምርታዊ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በክልሉ ሠላምን ለማጽናት በተሰጠው ትኩረት በምዕራብ ኦሞ እና ኮንታ ዞኖች አካባቢ ለረዥም አመታት የቆየ ቁርሾና አለመግባባቶች በእርቅ መፍታት መቻሉን አስረድተዋል።
ይሁን እንጅ ክልሉ በሚዋሰንባቸው አዋሳኝ አከባቢዎች የግጭት ስጋት መኖሩን እንዲሁም በአርብቶአደር በራሱ የሚስተዋሉ የውስጥ ግጭቶች ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ነው አቶ አንድነት የገለጹት።
በከተሞች አካባቢ ዘላቂ ሠላምን በማስፈን ዜጎች ሠላማዊ የእለት ተለት እንቅስቃሴ እንዲከውኑ ከማስቻል አኳያ የተሰራው ስራ አበረታች ቢሆንም መደበኛ ወንጀል የመከላከል ስራ ልዩ ትኩረት የሚፈልግ እንደሆነ አንስተዋል።
በታችኛው መዋቅር የሚሊሻ አደረጃጀት በማጠናከር የሚከሰቱ ወንጀሎችን በብቃት መመከት እንዲችሉ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
በመሆኑም የማይቀለበስ አደረጃጀት በመፈጠር በተልዕኮ የሚመራርና የህዝብ ባለቤትነት ያረጋገጠ የጸጥታ መዋቅር መገንባት አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
ፈጣንና ወንጀልን ቀድሞ የሚከላከል ጠንከራ የመረጃ ስርዓት መዘርጋት ለዘላቂ ሠላም ግንባታ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ አንድነት የወሳኝ ኩኔት ተግባር በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የቀበሌ ተደራሽ ለማስፋት ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።
የዞኖቹ የ2018 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በዞን መምሪያ ኃላፊዎች ለተሳታፊዎቹ እየቀረበ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊዎች፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ካሣ፣ የዞን መምሪያ ኃላፊዎች፣ የክልሉቢሮ እና ዞን መምሪያ ማኔጅመንት አባላት እና ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በጌታሁን ግርማ
