




የክልሉ ግብርና ቢሮ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ከምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለሁለት ተከታታይ ቀናት ለዞንና ለከተማ አስተዳደር የእንስሳት እርባታ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየው የከተማ ግብርና ፓኬጅ ስልጠና ተጠናቋል።
ስልጠናው በሌማት ትሩፋት ፓኬጅ አተገባበር፣ በዶሮ እርባታና ጤና አጠባበቅ፣ በወተት ፓኬጅ፣ በመኖ ልማት አዘጃጀትና አጠቃቀም ላይ ያተኮሩ የስልጠ ሰነዶች በቢሮው ከፍተኛ የዘርፉ ባለሙያዎች ቀርቦ በሰፊው ለዘርፉ ባለሙያዎች ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል ።
የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዕድል እየሰጡ ያሉት የከተማ ግብርና እና የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሮች በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ እየሆኑ ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑም በመድረኩ ተመልክቷል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የእንስሳትና ዓሣ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ በቀለ፤ ስልጠናው ለዘርፉ ባለሙያዎች የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠርና የከተማ ግብርናን ለማጠናከር የሚያግዝ እንደሆነና በቀጣይ የሰው ሃይል ክፍተቶችን በሟማላት በሁሉም ከተሞች ውጤታማ ለመሆን ትኩረት ተሰጥቶ እንደሰራም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የእንስሳት ፓኬጅ በአዲስ መልክ ወደ ትግባራ እንዲገባ ተደርጎ በከተማ ግብርና አርንጓዴ መኖ በአጭር ጊዜ ለማስፋት እየተሰራ ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑንና ይህንን ታሳቢ ያደረገ ስራ በሰፊ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የከተማውን ማህበረሰብ ከሸማችነት ወደ አምራችነት ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ በመጠቆም የከተማ ነዋሪዎች በሰፊው በማምረት ራስን በምግብ መቻልና ገበያውን ለማረጋጋት በሚደረገው ጥረት ወስጥ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም አቶ ታመነ አንስተዋል።
በከተሞች አካባቢ ዘመናዊ ግብርናን በማስፋት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል ትኩረት ተሰጥ እየተሰራ መሆኑንና ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።
የስልጠና ተሳታፊ ባለሙያዎችም ስልጠናው ያለብንን የእውቀትና ክህሎት ክፍተቶች የሚሞላ በመሆኑ የከተማ ግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ሳይንሳዊ ዘዴዎችን ለነዋሪዎች በማስረጽ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በከተሞች ላይ በከተማ ግብርና እና በሌማት ትሩፋት የተጀመሩ ውጤታማ ስራዎች መኖራቸውን አንስተው በተሻለ መልኩ በመስራት ዘርፉን ለማሻገር የሰው ሃይል፣ የበጀት፣ የድጋፍና ክትትል ላይ የሚታዩ ውስንነቶችን መቅረፍ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
