


የምክርቤት አባላት የቀረበው የአስፈጻሚ አካላት ሪፖርት የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት እንደሆነም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።
በክልሉ ታቅደው የተከናወኑ እና አዳሪ ፕሮጀክቶች ላይ የታየው የአፈጻጸም ለውጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም የምክርቤት አባላት አስተያየት ሰጥተዋል።
በተከናወኑ የልማት፣የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ልማት ስራዎች የበለጠ ውጤታ እንዲሆኑም ጥያቄዎችን የምክርቤት አባላት አንስተዋል።
ከተነሱት ጥያቄዎችም በትምህር ስራዎች አበረታች ውጤቶች ቢታዩም በአንጻሩ የ4ኛ ክፍል ፈተና አዘገጃጀት ፣የመምህራን ልማት ስራዎች እና የትምህርት ቤት ብሎክ ግራንት በወቅቱ አለመለቀቅና የትምህርት ውስጣዊ ብቃት ከማሻሻል አንጻር የሚስተዋሉ ክፍተቶች ሊታረሙ እንደሚገባ ተጠይቋል።
በክልሉ ወጥ ያልሆነ የትምህርት ግብዓት አቅርቦት መኖር የትምህርት ውስጣዊ ብቃትን ከማሻሻል አንጻር ተጽዕኖው ከፍተኛ በመሆኑ መስተካከል እንደሚገባው ተጠይቋል።



በጤናው ዘርፍ በርካታ ስራዎች የመሰራታቸውን ያህል ለተቋማት ግብዓት ከማሟላት አንጻር ፣ የተጀመሩ የጤና ተቋማት ግንባታ ያለመጠናቀቅ፣የወባ በሽታ አሁንም ፈተና መሆኑ ትኩረት የሚሻ ተግባር መሆኑንና፣በኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ተነስቷል።
በማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ከህብረተሰቡ የሚሰበሰቡ ገንዘቦች በተገቢው ወደ ባንክ አለመግባት ለአገልግሎት አሰጣጥ መሠረታዊ ችግር በመሆኑ ሊፈተሽ ይገባል ሲሉም የምክርቤት አባላት ጠይቀዋል።
በግብርና ልማት ስራዎች ጥራት ላይ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል፣በተለይም ምርትን ከማሳደግና የገበያ ትስስርን ከመፍጠር አንጻር በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ከምክርቤት አባላት ተጠይቋል።
የሌማት ትሩፋት ስራዎች በተሻለ ሁኔታ ተከናውነዋል ሆኖም ግን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስተያየት ተሰጥቶታል ።
በአርብቶ አደሩ አካባቢ በተለይም በመንደር የማሰባሰብ ስራው ያለበት ደረጃ እንዴት ተገምግሟል? የተጀመሩ የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በምክርቤት አባላት ተጠይቋል።
የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ የተከናወኑ ስራዎች የሚበረታቱ ቢሆንም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች አሁንም ትኩረትን የሚሹ ፕሮጀክቶች ተለይተው ሊሰሩባቸው እንደሚገባ ተነስቷል።
ከነባሩ ክልል የተሸጋገሩ የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ፕሮጀክቶች በየአካባቢው አለመጠናቀቁ በህዝብ ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል ፈጥኖ ማስተካከል ይገባልም ሲሉ ጠይቀዋል።



በመንገድና ድልድይ መሠረተ ልማቶች በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ትኩረትን የሚሹ ፕሮጀክቶች ፈጥነው ሊጠናቀቁ እንደሚገባና በፌዴራል መንግስት የተጀመሩ የአስፓልት መንገዶች አለመጠናቀቅ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየሆኑ መምጣታቸው ሊቀረፍ እንደሚገባ ተጠይቋል።
ከስራ ዕድል ፈጠራና ከዜጎች ተጠቃሚነት አንጻር የተጀመሩ ስራዎች እና የቁጠባ ባህልን የማጠናከር ስራዎች ዙሪያ ያሉ ዕጥረቶች ሊቀረፉ እንደሚገባ አስተያየት ተሰጥቶታል።
የከተማ ልማት ስራዎች በራስ አቅም መሠረተ ልማቶችን የመገንባት ልምድ ሊዳብር ይገባዋል፤በከተማም የመሬት አጠቃቀምን ስራ ማዘመን እንደሚገባ ተነስቷል።
የክልሉን ገቢ ከማሳደግ አኳያ በደረሰኝ አቆራረጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት ሊሰራበት ይገባልም ተብሏል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግሮችና የተቆራረጠ አገልግሎት በስፋት እየተስተዋለ በመሆኑ ሊቀረፍ እንደሚገባ ተጠይቋል።
በክልሉ የተጀመረው የሠላምና ጸጥታ ስራዎች የሚበረታቱ ሲሆን ዘላቂ ከማድረግ አንጻር አሁንም በልዩ ትኩረት ሊሰራበት ይገባል ሲሉም የምክርቤት አባላት ጠይቀዋል ።
በክልሉ የማዕድን ምርቶች የመኖራቸውን ያህል በተለይም ከወርቅ ምርት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች በዘላቂነት ሊቀረፉ እንደሚገባም ተጠይቋል።
የግብይት ማዕከላትን ከማጠናከር እና ዘመናዊ ግብይትን ከማሳለጥ አንጻር ገና የሚቀር ስራ ያለበት በመሆኑ ትኩረት ይሰጠው የሚል ጥያቄ በምክርቤት አባላት ቀርቧል።
በክልሉ የካርበን ልቀትን በመከላከል ረገድ ሁለት ባዮ ስፌር በዩኔስኮ ተመዝግበው ይገኛሉ ። በእነዚህ ሀብቶች የአካባቢዉን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ምነወ እየተሰራ ነዉ፤ሌሎች ተጨማሪ ባዮስፌር ለማስመዝገብ ምን ተደርጓል? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል ።
በታጠቅ አበበ
